የመዲናዋ የገቢ አሰባበሰብ አቅምን በማሳደግ የሰፊውን ሕዝብ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተሠራ ይገኛል – አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ

የመዲናዋ የገቢ አሰባበሰብ አቅምን በማሳደግ የሰፊውን ሕዝብ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተሠራ ይገኛል – አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ
AMN – ታኅሣሥ 10/2017 ዓ.ም
በአዲስ አበባ የገቢ አሰባበሰብ አቅምን በማሳደግ የሰፊውን የከተማ ሕዝብ የልማት ጥያቄ ለመመለስ እየተሠራ እንደሚገኝ የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
የገቢዎች ቢሮ በተያዘው በጀት ዓመት 230 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ አቶ ብንያም ምክሩ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ተናግረዋል።
ገቢውን በታቀደው መሠረት በመሰብሰብ መዲናዋን ለሕዝቡ ምቹ ለማድረግ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝ አቶ ብንያም ገልጸዋል።
ላለፉት አምስት ወራት ይሰበሰባል ተብሎ የታቀደው 104 ቢሊየን ብር መሆኑን አስታውሰው፣ እሰካሁን ከ92 ቢለየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን እና ይህም የዕቅዱን 89 በመቶ እንደሚሆን አክለዋል።
የገቢ መሠረቱን ለማስፋት ከዚህ ቀደም በታክስ ሥርዓት ውስጥ ያልገቡትን ነጋዴዎች ወደ ሥርዓቱ በማስገባት የከተማዋን ገቢ ለመጨመር በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኝ አቶ ብንያም ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማቱም ከገቢ አንጻር ተጨማሪ ሃብት ይዞ መምጣቱን ጠቁመው፣ ከተማው በመዋቧ እና ሕንፃዎችም ለንግድ ሥርዓት ምቹ በመደረጋቸው አዳዲስ የሥራ መስኮች ተፈጥራል ብለዋለ።
ይህም በኮሪደር ልማቱ ምክንያት አንዳድ ነጋዴዎች ከነበሩበት አካበቢ ተነሥተው ሌላ አካበቢ ላይ መደበኛ ሥራቸውን እስኪጀምሩ በመዲናዋ ገቢ ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር አግዟል ነው ያሉት።
በመዲናዋ የተጀመሩ ሰፊ የልማት ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ገቢ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ ይህንን ለማሳካት በመርካቶ የተጀመረውን የሕግ ማስከበር ሥራ አጠናክሮ ማስቀጠል አንዱ የቢሮው ሥራ እንደሆነ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የገቢ መሠረቱን የማስፋት ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የግብይት ሥርዓቱ በደረሰኝ ብቻ እንዲሆን ማድረግ በከተማዋ ገቢ መጨመር ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ይህንን አውቆ ለየትኛውም ግብይት ደረሰኝ መጠየቅን ባህል ማድረግ እንዳለበት አቶ ብንያም አሳስበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *