በመዲናዋ በ19 ስጋ ቤቶችና በ6 የግንባታ እቃዎች መሸጫ ቤቶች ላይ በተካሄደ ኦፕሬሽን 32 ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ የተገኙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡

ጥር 23 ቀን 2018ዓ.ም ፣ አዲስ አበባ፣ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የግብር ስወራን ለመከላከልና የንግድ ሥርዓቱን ፍትሀዊነት ለማረጋገጥና የህግ የበላይነትን ለማስከበር በተከናወነ የተጠና፣ የተቀናጀና ድንገተኛ ኦፕሬሽን በ25 የንግድ ድርጅቶች ደረሰኝ ሳይቆርጡ ግብይት ሲፈጽሙ የተገኙ 32 በስጋ ቤትና በግንባታ እቃዎች ንግድ ላይ የተሰማሩ ተጠርጣሪዎችን በህግ ቁጥጥር ስር ማዋሉን አሳወቀ።
ቢሮው ቅዳሜ ጥር 23 ቀን 2018ዓ.ም መርካቶን ጨምሮ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ባካሄደው የተጠና የኦፕሬሽን ተግባር በ2 የንግድ ዘርፎች በድምሩ 32 የንግድ ድርጅቶች በሕግ የተጣለባቸውን የደረሰኝ አጠቃቀም ግዴታ ባለመወጣት ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል ብሏል።
በዚህም ከድርጊቱ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸው የንግድ ስራዎቹ ባለቤቶችና ሽያጩን ያለደረሰኝ ሲያከናውኑ የነበሩ ሰራተኞች የመንግስትን ግብር ለመሰወር ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ ተገኝተው በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸውን አሳውቋል፡፡
የኦፕሬሽን ተግባሩ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ማካሄዱን የገለጸው ቢሮው በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች የመንግሰትን ጥቅም ለማሳጣት ከታክስ አስተዳደር አዋጅ በተፃረረ መልኩ ያለደረሰኝ ሽያጭ በመፈፀም ወንጀል ተጠርጥረው በአሁኑ ወቅት ጉዳያቸው በፖሊስ ተይዞ ለፍርድ የሚቀርቡ ይሆናል ብሏል፡፡
በቀጣይ ቀናትም ቢሮው የኦፕሬሽን ተግባሩን በሌሎችም ዘርፎች አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያሳወቀ ሲሆን የንግዱ ማህበረሰብ ግብይቶችን በደረሰኝ ብቻ እንዲፈፅም ህብረተሰቡም በ7075 ነፃ የስልክ መስመር በመጠቀም መሰል ወንጀሎችን እንዲያጋልጥ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ቢሮው ከዚህ ቀደም በጎማ፣ በኤሌክትሮኒክስና በኮንስትራክሽ ዘርፎች በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ ባካሄደው የተጠና ኦፕሬሽን 35 ተጠርጣሪዎች ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ ተይዘው በህግ ቁጥጥር ስር ማዋሉ ይታወሳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *