የተከበራችሁ የድረ-ገጻችን ጎብኚዎች/ግብር ከፋዮቻችን
በመጀመሪያ እንኳን ወደ ድረገጻችን በሰላም መጣችሁ
ቢሯችን በታክስ ህጎች፣ አዋጆች መመሪያዎች፣ የአሰራር ማንዋሎችና መሰል መረጃዎች በቀላሉ ለእናንተ በማድረስ ስለታክስ ያላችሁ ግንዛቤ እንድታሳድጉና በተቋማችን አገልግሎትና አሰራሮች ዙሪያ ገንቢ አስተያየቶችን በቀጥታ በተለያዩ መንገዶች በመስጠት ለተልዕኳችን በማሳካት የበኩላችሁን እንድትወጡ ይህንን ድረገጽ አልምተናል፡፡
በተጨማሪም ለታክስ አሰባሰብ ስርዓቱ ወሳኝ የሆናውን የሰው ሃብት ቅጥርን በ(online) ለመመዘግብ የሚያስችል ፎርም ያካተተ ሲሆን ቢሮውን ከባለድርሻ አካላት ጋር ለማገናኘት ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡
አስተዳደሩ ከሚሰራቸው የከተማችን ገጽታ የሚቀይሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶችንና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ጎን ለጎን በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ነዋሪዎችን ለመደገፍ በተለይም ታዳጊ ህጻናት ለማስተማርና ብሩህ ተስፋ እንዲኖራቸው ለማድረግ የጀመርነው የምገባ፣ የዩኒፎርምና የማስተማሪያ መሳሪያዎች የማቅረብ ስራ እየሰራን እንገኛለን፡፡ እነዚህ ስራዎች የሚሰሩት ከናንተ በሚሰበሰበው ገቢ ነው፡፡ በመሆኑም የምትከፍሉት ገቢ ለሀገር እድገትና ብልጽግና ያለው ፋይዳ በመገንዘብ ‶ለከተማዬ እድገት የበኩሌን ልወጣ‶ በሚል ሀገራዊ ወይም ወገናዊ ስሜት የሚጠበቅባችሁን ግብር በወቅቱ እንድትከፍሉ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡
ለሀገር መከላከያና በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ለመርዳትና ለማቋቋም የሚያደረገው ድጋፍ እንደተጠበቀ፣ ግብርን በወቅቱ በመክፈል ሀገራዊ ግዴታን ለመወጣት ሌት ተቀን የሚጥሩት ታክስ ከፋዮችን እውቅና በመስጠት፣ ምርጥ ተሞክሮን በመውሰድና በማመስገን ወደ ሌሎች ማስፋት የሚገባ ሲሆን፤ በግብር መሰወር፣ ህገወጥና ያለደረሰኝ ግብይት የሚፈጽሙና ግብርን ለመክፈል ፈቃደኝነት በማጣትና በሌብነትን የተሰማሩ ጥቂት ታክስ ከፋዮች በማጋለጥና በማረም እንደሀገር ብሎም እንደ ከተማ የጀመርነው የብልጽግና ጉዞን ማሳካት ይኖርብናል፡፡
የመዋቅሩ አመራሮችና ሰራተኞችም ከታክስ ከፋዩ ህብረተሰብ የምንሰበስበው እያንዳንዱ ብር ለብልጽግና ጉዞአችን ያለው ፋይዳና ይህንን መስረቅ ደግሞ ሀገርን ማፍረስና ትውልድን መግደል መሆኑን በመገንዘብ ራሳችሁን ከህገ ወጥ ስራ በመታቀብ፣ ሌሎችን በማረምና በማጋለጥ ሀላፊነታችሁ እንድትወጡ በዚህ አጋጣሚ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡
በመጨረሻም ይህንን ድረገጽም ሆነ ሌሎች ገጾቻችን በአግባቡ በመጠቀም የእርስ በርስ መገነባቢያ ውጤታማ የተግባቦት መንገዶች በማድረግ እንድንጠቀምባቸው አደራ እላለሁ፡፡
የላቀ ገቢ ለከተማችን ብልጽግና
አመሰግናለሁ
ክቡር አቶ ቢኒያም ምክሩአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ