ነሐሴ 07 / 2017 ዓ / ም የአዲስ አበባ፣ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በከተማዋ እያካሄደ የሚገኘውን የቁጥጥር ስራ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በማድረግ ከብልሹ አሰራር ለመከላከል የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱን በትላንቱ ዕለት ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
የዝግጅት ክፍላችንም በዛሬው ዕለት በመርካቶ አካባቢ በመገኘት የንግዱ ማህበረሰብን ቢሮው ወደ ተግባር ባሸጋገር በቴክኖሎጂ የታገዘ የቁጥጥር ስርዓት ላይ ያላቸውን አስተያየት አሰባስቧል፡፡
በመርካቶ በፌስታል ንግድ ላይ ተሰማርተው የሚገኙት ወይዘሮ ሐያት አብድላ ቢሮው ይፋ ያደረገው አሠራር በተለይም በመርካቶ የገቢዎች ሰራተኛ ያልሆኑ ከገቢዎች ነው የመጣነው በማለት ያልተገባ ድርጊት የሚፈጽሙ ፣ ግብር ከፋዩን የሚያስጨንቁና አጭበርባሪዎችን ለመከላከል የሚያስችል ነው ብለውናል፡፡
ቢሮው ለቁጥጥር ባለሙያዎቹ ዩኒፎርም ማስለበሱም ከዚህ ቀደም በተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ይስተዋሉ የነበሩ ብልሹ አሰራሮችን ሊከላከል እንደሚችል ነግረውናል።
ተቆጣጣሪዎችም የገቢዎች ቢሮ ሰራተኛ ስለመሆናቸው ለመለየትና ብልሹ አሰራሮችን ለማጋለጥ የሚረዳ ነው ብለዋል ።
በሌላ በኩልም በቢሮው ሰራተኞች ስም የሚፈፀሙ የማጭበርበር ወንጀሎችን ለመከላከልና ለሚመለከተው አካል በመጠቆም በህግ ቁጥጥር ስር በማዋል የንግዱ ማህበረሰብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ላይ አቶ አልፋሳ ነጋሽና አቶ ሙሀረዲን ሙሳ በበኩላቸው ለደረሰኝ ቁጥጥር ባለሙያዎች ቢሮው መለያ ዩኒፎርም ማዘጋጀቱ ከዚህ ቀደም በቢሮው ሰራተኞች ስም የሚፈፀም ማጭበርበር የሚቀርፍ በመሆኑ ሌሎችም ተቋማት እንደተሞክሮ ሊወስዱት እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
በኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ ሬድዋን ጀማል በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የቁጥጥር ባለሙያዎች ማንነት መለየት ስለማንችል ‹‹የገቢዎች ሰራተኛ ነን እያለ ማንም መጥቶ ያጭበረብረን ነበር እኛም የምንለይበትን ሁኔታ ባለመኖሩ የመጣ ሁሉ የገቢዎች ቢሮ ሰራተኛ መስሎን በቢሮው እንማረር ነበር፡፡ ከዚህ በኃላ ግልጸኝነት የሚፈጥር አሰራር በመዘርጋቱ ደስተኛ ነን›› ሲሉ ነው የነገሩን፡፡
በንጽሕና እቃዎች ንግድ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ኤልዳና ሺፈራው በበኩላቸው ባርኮድ የተካተተበት የቁጥጥር ባለሙያዎች መታወቂያ በእጅ ስልካችን ስካን በማድረግ ማንነታቸውን በቀላሉ ለመለየትና የቢሮው ትክክለኛ የቁጥጥር ባለሙያዎች መሆናቸውን ለመለየት አሰችሎናል ብለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የቁጥጥር ባለሙያዎች መለያ ይዘው እንዲቀሳቀሱ ማድረጉ በተለያየ ምክንያት ከገቢዎች ቢሮ የተባረሩ ባለሙያዎችና ሌሎች አጭበርባሪዎች በመተባበር ክፍተቶቻችንን መሰረት በማድረግና በማስፈራራት የሚያደርሱብን ጫና እና የሚጠይቁን የእጅ መንሻ ለመከላከል የሚረዳ ነው ሲሉ ነግረውናል፡፡