የቁጥጥር ባለሙያዎች ፍትሃዊ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት ለመዘርጋት ቢሮው የሚያደርገው ጥረት እንዲሳካ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2018 በጀት ዓመት የተጠናከረ የሕግ ማስከበርና የቁጥጥር ስራ ፍትሃዊነት ላይ በማተኮር የሚተገበር መሆኑን ነው በዛሬው ዕለት ከቁጥጥር ሰራተኞች ውይይት በተካሄደበት ወቅት የተገለፀው።

በመድረኩ የቢሮው ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ በ2017 በጀት አመት ከገቢ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸው ገልፀዋል።

በበጀት ዓመቱ ለተመዘገው ውጤትም በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ፈጻሚ ተቀናጅቶ መስራት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል።

በበጀት አመቱ ከተሰበሰበው ገቢ 71 ከመቶው ለዘላቂ ልማትና ለሰው ተኮር ተግባራት እንዲሁም የከተማዋን ተወዳዳሪ ለሚያደርጉ ፕሮጀክቶች የዋለ መሆኑን ተናግረዋል።

በ2018 በጀት ዓመትም የቁጥጥር ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን በፍትሃዊነት መርህ በታማኝነት ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

መልካም ስነ ምግባር የቢሮው የቁጥጥር ባለሙያዎች መገለጫ ሊሆን ይገባል ያሉት ኃላፊው በተለይ ለግብር ከፋዩ ተገቢውን ክብር መስጠት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የቁጥጥር ባለሙያዎች ተግባሮቻቸውን በሚወጡበት ወቅት ለግብር ከፋዩ ማንነታቸውን በአግባቡ ማሳወቅ ይጠበቃልም ብለዋል።

በቢሮው የሚተገበሩ የህግ ማስከበር ስራዎች በሙሉ በፍትሃዊነትና በእኩልነት መርህ ላይ ሊመሰረቱ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በ2018 በጀት ዓመት ያቀደው የ350 ቢሊዮን ብር የገቢ እቅድ ለማሳካት በመርካቶና በከተማዋ የተለያዩ የገበያ ቦታዎች ላይ የተጀመረው የህግ ማስከበር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አክለው ተናግረዋል።

በመሆኑም ከተማዋ ለልማት የሚያስፈልጋት ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ የቁጥጥር ባለሙያዎች ሚናቸው የማይተካ መሆኑን በመገንዘብ ኃላፊነታቸውን በብቃትና በውጤታማነት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በህጋዊ መንገድ ደረሰኝ በመቁረጥ የሚሰሩ ግብር ከፋዮችን ማበረታታት ህገወጦችን ደግሞ ወደ ህጋዊ ስርዓት መመለስ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ቢሮው በከተማ አስተዳደሩ የተሰጠውን ተልዕኮ በውጤታማነት ለማሳካት በአንድ በኩል ፍትሃዊ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት በመዘርጋት በሌላ በኩል ደግሞ የገቢ መሰረት ለማስፋትና የህግ ማስከበር ስራዎች በውጤታማነት ለመፈፀም የሚያስችሉ አሰራሮች፣አደረጃጀቶችና ቴክኖሎጂዎች በማልማት እየተተገበሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በቢሮው የህግ ማስከበር ዘርፍ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚኪያስ ሙሉጌታ በበኩላቸው ቢሮው የህግ ማስከበር ስራዎቹን ለማጠናከር የመርካቶ አደረጃጀትን ሙሉ በሙሉ በመለወጥ በህግ ማስከበር ስራ ላይ ትኩረት በማድረግ እንዲሰሩ የሚያስችል አደረጃጀት ወደ ተግባር ማሸጋገሩ ገልፀዋል፡፡

በመርካቶ የተመደቡ ቁጥጥር ባለሙያዎችም ግብር ከፋዩ በግልፅ እንዲያውቃቸው የሚያስችል ልዩ ኮድ የተካተተበት ዩኒፎርም የሚለብሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የቁጥጥር ባለሙያዎች ለቁጥጥር በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ማንነታቸውን የሚገለፅ ባርኮድ የተካተተበት መታወቂያ በመያዝ ለግብር ከፋዩ በግልፅ ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

በከተማችን የሚገኙ ግብር ከፋዮች ማነኛውም ግዢም ሆነ ሽያጭ በሚያከናውንበት ጊዜ በደረሰኝ ብቻ መሆን እንዳለበትና ለዚህም ስራ ስኬታማነት የንግዱ ማህበረሰብም ሆነ የከተማው ነዋሪ የጋራ ሀላፊነት እንዳለበት በመድረኩ ላይ በአፅንዖት ተነስቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *