ነሐሴ 13 / 2017 ዓ / ም የአዲስ አበባ፣ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የቁጥጥር ስራው በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ማድረጉ ሌብነትና ብልሹ አሰራሮችን ከመከላከልና የአሰራር ግልጽነት ከመፍጠሩም ባሻገር ሕጋዊውና ሕገወጡን በቀላሉ መለየት የሚያስችል በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በመርካቶ በመደብራቸው ሲሰሩ ያገኘናቸው ነጋዴዎች ገለጹ ፡፡
የዝግጅት ክፍላችን በመርካቶ አካባቢ በመዘዋወር ቢሮው ወደ ተግባር ባሸጋገር በቴክኖሎጂ የታገዘ የቁጥጥር ስርዓት ላይ የታክስ ከፋዮች አስተያየት አሰባስቧል፡፡
በመርካቶ በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ላይ ተሰማርተው የሚገኙት አቶ ከዲር መሐመድ ቢሮው ይፋ ያደረገው የቴክኖሎጂ አሠራር አብዛኛው ነጋዴ እፎይታ የሰጠውና ከዚህ በፊት የነበረው የተዘበራረቀ የቁጥጥር ስራ ፈር ማስያዙን ገልጸዋል ፡፡
አሰራሩ ሕጋዊ ያልሆኑና ወደ ታክስ መስመሩ ያልገቡ ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊ መስመር የሚያሲዝ መሆኑን ጠቅሰው በቢሮው ስም የሚያጭበረብሩ ወንጀለኞችን ለመከላከልና ለማጋለጥ የሚያስችል እንደሆነም ለዝግጅት ክፍላችን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረው አሰራር ነጋዴው የሚያስጨንቅና ህጋዊ በህጋዊነቱ እንዲቀጥል ከማድረግ ይልቅ ሕገ ወጥ እንዲሆን የሚገፋፋ እንደነበረው በማውሳት ቢሮው አገልግሎቱ ለማዘመን እየሰራ የሚገኘው ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል ይኖርበታል ብለዋል ፡፡
በሳሙና ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ ያሳብ አንማው በበኩላቸው አዲሱ ቴክኖሎጂ በቢሮውና በቁጥጥር ሰራተኞች ስም የሚፈፀሙ የማጭበርበር ወንጀሎችን ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑን ገልጸው ታክስ ከፋዩ የቁጥጥር ባለሙያዎች እንዲያስተካክሉ የሚነግሯቸው ጉዳዮች ትኩረት ሰጥተው እንዲያስተካክሉም አሳስበዋል፡፡
በኮስሞቲክስ ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ እዮብ አብዶ አሰራሩ እጅግ በጣም ጥሩ መሆኑን በጠቅሰው ባርኮድ የተካተተበት የቁጥጥር ባለሙያዎች መታወቂያ በእጅ ስልካችን ስካን በማድረግ ማንነታቸውን በቀላሉ የቢሮው ትክክለኛ የቁጥጥር ባለሙያዎች መሆናቸውን የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል ፡፡
አያይዘውም አሰራሩ በቢሮው ስም የሚፈፀሙ የማጭበርበር ሕገወጦችን በመከላከል ሕጋዊውን ነጋዴ ይበልጥ የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።