ነሐሴ 28 / 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2018 በጀት ዓመት አጥንቶ ወደ ተግባር ባሸጋገራቸው 24 አሰራሮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በመግለጫው የቢሮው የታክስ ውሳኔ ቅሬታ ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ ደጌ ቢሮው ግብር ከፋዮች በተለያዩ ጊዜያት የሚያነሷቸው የመልካም አስተዳደር፣ የሌብነትና ብልሹ አሰራሮችን ለመዝጋት በየጊዜው የማሻሻያ አሰራሮችን ለግብር ከፋዩ ማሕበረሰብ ተደራሽ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
በቢሮው የተዘረጉ እነዚህ አሰራሮችም በግብር ከፋዩና በገቢ ሰብሳቢው መስሪያ ቤት መካከል ያለውን ግንኙነት ሊያሻሽሉ፣ የግልፀኝነትና የተጠያቂነት አሰራር የሚያጠናክሩ ናቸው ያሉት አቶ ኤርሚያስ ከዚህ ቀደም በታክስ ኦዶት ውሳኔ አሻሚ የሆኑ ጉዳዮች በመቅረፍ ግልፅ አሰራር ላይ መሰረት ያደረገ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችሉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በቢሮው የተዘረጉ አሰራሮች ግብር ከፋዩ ሕብረተሰብ የግብር ግዴታውን በሚወጣበት ወቅት ትኩረት ማድረግ ያለባቸው ነጥቦች የሚያመላክቱ ናቸውም ሲሉም ገልፀዋል፡፡
የተዘረጉ አሰራሮች ዋነኛ ዓላማዎችም ግልፅ የግብር አሰባሰብ ስርዓት በመዘርጋት ግብር ከፋዩ ራሱን ካላስፈላጊ የታክስ ዕዳዎች ፣ የታክስ ማጭበርበርና የህግ ተጠያቂነት መጠበቅ መሆኑን በአፅንኦት ገልፀዋል ።
ከዚህም በተጨማሪ በግብር ከፋዮች በተደጋጋሚ የሚነሱ ቅሬታዎች መነሻ በማድረግ በተመረጡ 10 ዘርፎች ችግሮን ለመውጣት ያስችላሉ ብለዋል፡፡
አክለውም የተዘረጉ አሰራሮች ነሁሉም ዘርፎች ሊተገበሩ ይገባል በሙል የተለዩ ጉዳዮች ያስቀመጠ ሲሆንግብር ከፋዩ እራሱን ካላስፈላገ ዕዳ ለመጠበቅ የሚረዱ መሆናቸውንም አመላክተዋል፡፡
አዲስ ወደ ንግድ ስርዓት የሚገቡ ግብር ከፋዮችም ከሂሳብ መዝገብ ጋር በተያያዘ የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመቅረፍ የሚረዳ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ በበኩላቸው በ2018 በጀት ዓመት በከተማ ደረጃ 350 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን በማንሳት እቅዱን ለማሳካት ለግብር አሰባሰብ ስርዓቱ እንቅፋት የሆኑ የአሰራር፣ አደረጃጀት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና እና የሰው ኃይል ችግሮችን በመፍታት ወደ ስራ እየተሸጋገሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
የአሰራር ስርዓቶቹ በታክስ አስተዳደር ሂደት የግብር ከፋዩ መብትና ኃላፊነት ለማሳወቅ በታክስ ባለስልጣኑ፣ በግብር ከፋዩ እና የግብር ከፋዩን ሒሳብ በሚያዘጋጁ ባለሙያዎች መካከል ግልጸኝነትን በመፍጠር ፍትሐዊነትን ማስፈን ታስቦ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ቢሮው ወደ ተግባር ያሸጋገራቸው አሰራሮች ለግብር ከፋዩ፣ ለሂሳብ ባለሙያዎችና ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ተደራሽ ለማድረግ በመፅሔት መልክ በማሳተም እያሰራጨ ይገኛል ያሉት አቶ ሰውነት በሶፍት ኮፒ ደግሞ በተቋሙ ድህረገፅ፣ ቴሌግራሞችና ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች መጫኑንም አመላክተዋል፡፡