በ123 የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ ቁጥጥር በማድረግ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወሰደ ፡፡

ነሀሴ 29 / 2017ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፣ገቢዎች ቢሮ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በሁሉም የከተማዋ አቅጣጫዎች ወደከተማዋ የሚገቡ፣ከከተማዋ የሚወጡና በከተማዋ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ፣ሚኒባሶችና ኣነስተኛ ሽፍን መኪኖች ላይ የመኪና ኦፕሬሽን ስራዎችን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየቀኑ ከተቋቋሙ ግብረ ሀይሎች ጋር በመሆን የደረሰኝ ቁጥጥሩን አጠናክሮ መቀጠሉ ታውቋል

ቢሮው በጥብቅ ከዕለት ወደዕለት እያካሄደ ያለው የመኪና ኦፕሬሽን ስራ ተሽከርካሪዎቹ ጭነው የሚንቀሳቀሱት ልዩ ልዩ ሸቀጦች፣ምርቶችና የኮንስትራክሽን ግብአቶች በህጋዊ ግብይት በደረሰኝ የተፈፀሙ ስለመሆናቸው ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑም ይታወቃል ፡፡

በዚህም ቀደም ተብሎ ከተሰሩ ቁጥጥሮች ባሻገር ከተቋቋሙ ግብረ ሀይሎች ጋር በተካሄዱ የቁጥጥር ስራዎች በየካ ክፍለ ከተማ 41 ፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ 28 ፣ በጉለሌ 44 ፣ እንዲሁም በቂርቆስ 10 ተሸክርካሪዎች ላይ ዕለታዊ ደረሰኝ ሳይዙ በከተማዋ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተው አስተዳደራዊ የቅጣት እርምጃ እና ለጫኑት እያንዳንዱ ዕቃም ደረሰኝ እንዲቆርጡ መደረጋቸው የዝግጅት ክፍላችን ባሰባሰበው መረጃ ለማወቅ ተችሏል ፡፡

በቀጣይም በከተማዋ ጭነት የጫኑ ማንኛውም አይነት ተሽከርካሪዎች፣ ተሳቢዎች፣ ሚኒባሶች እና ሽፍን መኪኖች ለጫኑት እቃ ዕለታዊ ደረሰኝ የተቆረጠበት መረጃ ስለመያዛቸው የማረጋገጥ ተግባር በከተማዋ በሁሉም ቦታ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ ተገልፆል፡፡

በቢሮው እየተካሄደ የሚገኝ የመኪና ላይ የቁጥጥር ስራ ዋነኛ ዐላማ በሁሉም አቅጣጫዎች ላይ የተለያዩ የኮንስትራክሽን ግብአቶች ፣ሸቀጦች እና የምግብ ምርቶችን ከቦታ ቦታ በሚያንቀሳቅሱበት ጊዜ ደረሰኝ እንዲይዙ የማድረግ ስራ መሆኑም ተመላክቷል

ቢሮው ትልልቅም ይሁኑ ትንንሽ መኪኖች እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ከተቋቋመው ግብረ ሀይልና ከከተማው ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ጋር በመቀናጀት ደረሰኝ ስለመያዛቸው የማረጋገጥና ያልያዙት ላይ አስተዳደራዊ ቅጣት በመቅጣት ለእያንዳንዱ ለጫኑት እቃ ደረሰኝ እንዲቆርጡ የማድረግ ስራን አጠናክሮ ቀጥሎበታል ።

ስለሆነም ማነኛውም የተሽከርካሪ ባለቤትና አሽከርካሪ እንዲሁም ነጋዴ በመኪና ላይ ጭኖ ለሚያንቀሳቅሰው ማነኛውም ምርት በዕለቱ የተቆረጠ ደረሰኝ የመያዝና ለከተማው የገቢዎች ቢሮ የቁጥጥር ሰራተኞች የማሳየት ሀላፊነት እንዳለበት ቢሮ አሁንም በአፅንኦት አሳስቧል።

የመኪና ላይ ህጋዊ የግብይት ደረሰኝ ቁጥጥር በመዲናዋ በሁሉም ቦታ ቀን በቀን ተጠናክሮ መቀጠሉንና ውጤትም እየተገኘበት መሆኑን ቢሮው አስታውቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *