ጳጉሜ 03 / 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ
የነዋሪዋ የልማት ፍላጎትና የከተማዋ ፈጣን ዕድገት ከለውጡ ወዲህ ከአመት አመት በመጨመሩ በገቢ አሰባሰቡ ከፍተኛ እምርታ መምጣቱ ተገለፀ ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የህግ ተገዢነት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ ሚኪያስ ሙሉጌታ ከቢሮው የኮሙንኬሽን ዳይሬክቶሬት ዝግጅት ክፍል የጳጉሜን 3 ” እምርታ ለዘላቂ ከፍታ ” በሚል የሚከበረውን የጳጉሜ ቀንን በማስመልከት ቆይታ አድርገዋል
ከለውጡ በፊት በ2010 ዓመታዊ ገቢ 34 ቢሊዮን እንደነበር ያነሱት ሀላፊው ዛሬ ላይ ለውጡ ባመጣቸው ፍሬዎች በ2017 በጀት አመት ከ233 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን እና ከተማዋው እምርታዊ የብልፅግና ለውጥ ማምጣቷን ተናግረዋል
የከተማ አስተዳደራችን የሚያከናውናቸው የሰው ተኮር ልማቶችና ሜጋ ፕሮጀክቶች የገቢ ምንጩ የከተማዋ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው በሚሰበሰብ ገቢ መሆኑ እና ከአመት አመት የገቢ ዕድገት እምርታ ማሳየቱን ገልፀዋል ።
የጳጉሜ 3 ቀናት ” እምርታ ለዘላቂ ከፍታ ” ስያሜ ተገቢነትን የገለፁት አቶ ሚኪያስ አልቆና ልቆ መፈፀም ነገን ይበልጥ ማንሰራራት እንደሚቻል አመላካች መሆኑንም ጠቁመዋል።
በያዝነው 2018 በጀት አመት በከተማ አስተዳደሩ የታቀደውን 350 ቢሊየን የገቢ ዕቅድ ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን ፣ በ2ወሩ ጥሩ እምርታዊ ለውጥ መታየቱንና ለዚህም ቢሮው የታክስ ( ግብር ) አሰባሰብ መሠረቱን ማስፋት ስራ እየሰራ መሆኑ ተናግረዋል ።
በሌላ መልኩ ወደ ታክስ ( ግብር ) ስርዐቱ ያልገቡትን የህግ ማስከበር ስራችንን በአሰራር አጠናክረን ቀጥለናል ያሉት አቶ ሚኪያስ ወደ 24 የሚደርሱ አሰራሮች ተዘርግተው ወደ ተግባር በማሸጋገር በግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የሚነሱ የሌብነት ፣ ብልሹ አሰራሮች ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲሁም የገቢ አሰባሰቡን አቅም የሚያዳክሙ ተግባራቶችን በጥናት በመለየት ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል ።
እምርታችን የበለፀገ ሀገር ለማስቀጠል እና የብልፅግና ተምሳሌት ከተማን እውን እያደረጉ መሄድ በመሆኑ ለታቀደው የላቀ ገቢ መሳካት በየደረጃው ያለው ሁሉም የባለድርሻ አካላት ሚናውን በተጠያቂነት እና በሀላፊነት ሊወጣ ይገባል ሲሉ ሀላፊው አብራርተዋል።
የከተማችን በየደረጃው ያሉ ግብር ከፋዮቻችን በታማኝነት ግብራቸውን በመክፈል አሁንም በከተማችን ሁለንተናዊ ልማትና የብልፅግና ጉዞ ላይ የማይተካ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ እና ግዴታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል ።
የታክስ መሠረቱን በማስፋት የታክስ ( ግብር ) የመሠብሰብ አቅማችንን ከአመት አመት ማሳደግ እና ማጠናከር ይገባናል ያሉት አቶ ሚኪያስ ምክንያት ያሉትንም አስቀምጠዋል ።
በዋነኛነት ሸማቹ ማህበረሰብ በግብይት ወቅት በደረሰኝ መገበያየት ፣ ደረሰኝ የመጠየቅና የመቀበል ባህሉን ሁሌ ማሳደግ እንዳለበትና የሚጠይቀው የልማት ፍላጎትን ለማሳካት የሚቻለው ከተማዋ በራሷ ገቢ የምትተዳደርና በምትሰበስበው ገቢ እንደሆነ ማመን አለበት ብለዋል ።
በመጨረሻም የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድን ለማሳካት ፣ እምርታዊ ለውጥን ለማምጣት እና ከተማችንን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ እየሰራን ነው ያሉት አቶ ሚኪያስ ቢሮው ወደ 24 የሚሆኑ አሰራሮቹን ዘርግቶ ወደ ተግባር ማሸጋገሩንም በአፅንኦት ገልፀዋል