መስከረም 07 / 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2018 በጀት አመት የታክስ ፍትሀዊነት በማረጋገጥ ፣ ከሌብነት ፣ ብልሹ አሰራሮችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመላቀቅ ገቢን በላቀ ደረጃ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ 24 የሚደርሱ አሰራሮች በመዘርጋት ወደ ተግባር ማሸጋገሩ ይታወቃል ፡፡
በዛሬው ዕለትም ከቅርንጫፎችና ወረዳዎች ጋር ባካሄደው የግምገማ መድረክ የበጀት ዓመቱ የ2 ወራት የገቢ ዕቅድ ከታክስና ከህግ ተገዢነት ዘርፍ፣ ከአገልግሎት አሰጣጥና ከሌብነትና ብልሹ አሰራርን ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች በመገምገም በጥንካሬና በክፍተት የተለዩ አፈፃፀሞች ላይ ተወያይቶ በመስከረም ወር የሚሰሩ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን ይፋ አድርጓል።
መድረኩን የመሩት የቢሮው ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ በሀምሌ ወር የደረጃ ‹‹ሐ›› እንዲሀም በነሀሴ ወር የግብር ግዴታቸውን መወጣት ከሚጠበቅባቸው የደረጃ ‹‹ለ›› ግብር ከፋዮች መካከል ዓመታዊ የግብር ግዴታቸውን ያልተወጡ ግብር ከፋዮችን በልዩ ትኩረት በመከታተል ግዴታቸውን እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ከመስከረም ወር ጀምሮ ደግሞ የደረጃ ‹‹ሀ›› ግብር ከፋዮች ቢሮው ቀልጣፈና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ በተዘረጋ የመስተንግዶ ፕሮግራም መሰረት ብቻ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
የደረጃ ‹‹ሀ›› ግብር ከፋዮች ሆነው ወደ ቫት መግባት እየተገባቸው ያልገቡ ግብር ከፋዮችን የማስገባት ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል እንሚገባ የገለፁት አቶ ቢኒያም በአዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ 1395/2017ዓ.ም መሰረት በስምንት የስራ ዘርፎች ውስጥ የሚገኙ 7 ሺህ 434 ግብር ከፋዮችን በፍጥነት ወደ ቫት ስርዓት ማስገባት ይገባል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይም በሞሎችና የኮሪደር ልማት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የተከፈቱ የንግድ ድርጅቶችን ወደ ቫት የማስገባት እንዲሁም የደሞዝ ገቢ ግብር የማይከፍሉ የፒኤልሲ (PLC) እንዲሁም የደረጃ ‹‹ሀ›› ግብር ከፋዮችን ወደ ክፍያ ስርዓቱ የማስገባት ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የታክስ ዕዳን በተመለከተም ጠንካራ ክትትል በማድረግ ዕዳውን በአግባቡ ለመሰብሰብ ዕዳ ማካካሻ ሊውል የሚችል ቋሚ የተሸከርካሪ፣ የቤት ንብረትና ሀብት በማፈላለግ የመንግስትና የህዝብ ጥቅም ማስጠበቅ እንደሚገባም አሳበዋል፡፡
ከህግ ማስከበር ስራዎች ጋር በተያያዘም የተጀመረው የተሸከርካሪዎች ቁጥጥር እንዲሁም መደበኛ የደረሰኝ ቁጥጥር ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የገለፁ ሲሆን የቁጥጥር ስራው በመደበኛ የስራ ሰዓት ብቻም ሳይሆን ሰራተኞች በሽፍት በመመደብ በማለዳና በማታ ጭምር የሚካሄድበትን አቅጣጫ መከተል ይገባልም ብለዋል፡፡
ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያም ለግብር ከፋዮቻችንን ተገቢውን ክብር በመስጠት በአግባቡ ማስተናገድ እንደሚገባ በመግለፅ ግብር ከፋዮችን የሚያመናጭቁ፣ በአግባቡ አግልገሎት የማይሰጡ፣ የማያዳምጡ፣ በመደበኛ የስራ ሰዓት በስራ ገበታቸው የማይገኙ ፈፃሚዎችና አመራሮች ላይ የዲሲፒሊን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም አሳበዋል፡፡
ከብልሹ አሰራሮችን ጋር በተያያዘም በቢሮው የወረዱ አሰረሮች በመሸራረፍ፣ የኦዲት ስራዎች ላይ የጥራትም ሆነ የሽፋን ጉድለቶች በመፈፀም፣ የግብር ግዴታቸውን ላልተወጡ ግብር ከፋዮች የክሊራስ አገልግሎት በመስጠት፣ የታክስ ማዕከል በማዞር ቫት በማሳወቅና በመሳሰሉ የሚገለፁ ብልሹ አሰራሮች የሚስተዋሉ መሆናቸው በመጠቆም በቅርንጫፍ ፅ/ቤትም ሆነ በወረዳ ደረጃ ያሉ አመራሮች ስራዎችን በቅርበት በመምራትና የተጠያቂነት ስርዓትን በማስፈን ችግሮቹን በፍጥነት ማረም ይገባል ብለዋል፡፡