የፈረንሳይ የልማት ድርጅት(AFD) ለገቢዎች ቢሮ በንብረት ታክስ (Property tax) አተገባበር ላይ ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገለፀ፡፡

መስከረም 26 ቀን 2018ዓ.ም ፣ ገቢዎች ቢሮ፣

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በዛሬው ዕለት ከፈረንሳይ የልማት ድርጅት ልዑካን ቡድን ጋር በንብረት ታክስ አስተዳደር፣ የትግበራ ሂደትና ድጋፍ ላይ ውይይት አካሄደ፡፡

በውይይቱ የቢሮው ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት 5 ዓመታት በገቢ ዘርፉ ተጨባጭ ለውጦችን ለማስመዝገብ መቻሉን ለልዑካን ቡድኑ ገልፀዋል፡፡

በዚህም በ2010 ዓ.ም በከተማ አስተዳደደሩ የሚሰበሰበው ገቢ ከ33 ቢሊዮን ብር የማይበልጥ እንደነበር በማንሳት በ2017 በጀት ዓመት 232.6 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መቻሉን አብራርተዋል፡፡

ቢሮው ባለፉት ዓመታት በቫት፣ በደሞዝ ገቢ ግብር እንዲሁም በቤትና ጣሪያ ግብር ላይ የተመዘገቡ ለውጦች በማሳያነትም አቅርበዋል፡፡

ከቤትና ጣሪያ ወይም የንብረት ግብር ጋር በተያያዘ በ2011 የግብር ከፋዮች ቁጥር ከ182 ሺህ የማይበልጥ እንደነበር ያነሱት ኃላፊ በ2016/17ዓ.ም የግብር ከፋዩን ቁጥር ወደ 483 ሺህ ለማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

ከቤትና ጣሪያ ግብር ጋር በተያያዘም የከተማዋ አቅም ከዚህም በላይ ነው ያሉ ሲሆን በዚህ ረገድ የሚስተዋል የመረጃ ክፍተት ሰፊ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም በገቢ ዘርፉ የሚስተዋል የአሰራር፣ አደረጃጀትና የቴክኖሎጂ አተገባበር ችግሮች በመቅረፍ ለከተማዋ ልማት የሚውል ገቢ በብቃት ለመሰብሰብ ቢሮው የተለያዩ ሪፎርሞች በማጥናት ወደ ተግባር እያሸጋገር ይገኛል ብለዋል፡፡

ስለሆነም የፈረንሳይ ልማት ድርጅት (AFD) በዚህ ረገድ ቴክኖሎጂን በማልማት እንዲሁም ብቃት ያለው ሰው ኃይል በስልጠና በማብቃት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፈረንሳይ ልዑክ ቡድን መሪ ሚስተር ጂን ቢኖት ፔሮት ሚኖት በበኩላቸው ድርጅታቸው ቢሮው በከተማዋ የንብረት ታክስን በብቃት ለመሰብሰብ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

የልማት ድርጅታቸው በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን፣ በንብረት ሀብት ምዝገባ፣ በመረጃ አሰባሰብና ማኔጅመንት እንዲሁም በሰው ኃይል አቅም ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ ፕሮጀክት በመቅረፅ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በማንሳት ፕሮጀክቱን በቀጣዮቹ 4 ወራት ወደ ተግባር ለማሸጋገር በጋራ ይሰራል ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *