ጥቅምት 3/2018ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፣ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ አመራሮችና ሰራተኞች በዛሬው ዕለት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከበረውን 18ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን የብሄራዊ መዝሙር በመዘመርና ቃለ መሀላ በመፈፀም ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ አክብረው ውለዋል፡፡
በክብረ በዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የቢሮው ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አዳኔ ሱሌ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን የምናከብረው በእኛ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሰንደቅ ዓላማ ትልቅ ስፍራ ያለው በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ዜጎች ለአገራቸው ያላቸውን ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት ለሰንደቅ ዓላማ በሚሰጡት ክብር ይገልፃል ያሉት ኃላፊው ሰንደቅ ዓላማችን የመስዋዕትነት፣ የሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት፣ የስነ-ልቦና፣ የፖለቲካ ታሪክ፣ የአብሮነትና የብሔራዊ መግባባት መገለጫ ዓርማ ምልክታችን በመሆኑ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር መስጠት፤ የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ አለበትም ብለዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር እኛ ኢትዮጵያዊያን ለሰንደቅ ዓላማ የምንሰጠው ክብርና ፍቅር ከእናት አባቶቻችን በክብር ወርሰን በክብር ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፈው በልባችን ውስጥ ታትሞ የሚቆይ የብዝኃነታችን፣ የአንድነታችንና የሉዓላዊነታችን መገለጫ ታላቅ አገራዊ እሴት በመሆኑ ጭምር መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
ስለሆነም የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች ለሰንደቅ ዓላማ የሚንሰጠው ክብር በተሰማራንበት የስራ መስክ ውጤታማ በመሆንና ተልዕኳችንን በአግባቡ በመወጣት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
የዘንድሮ ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ልዩ የሚያደርጉ ሀገራዊ ሁነቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ኃላፊው የህሱ ግድባችን በተመረቀ ማግስት የሚከበር መሆኑ በማሳያነት አንስተዋል፡፡
በከተማችን የተጀመሩ የልማት ውጥኖች ከዳር እንዲደርሱን እንደገቢዎች ቢሮ እጅ ለእጅ ተያይዘን ለሰንደቅ ዓላማችን የተከፈለውን መስዋዕትነት በመድገም የዘመናችንን ታሪክ ልንሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡