ጥቅምት 05 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2018 በጀት አመት የታቀደውን ገቢ የታክስ ፍትሀዊነት በማረጋገጥ ፣ ከሌብነት ፣ ብልሹ አሰራሮችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመላቀቅ ገቢን በላቀ ደረጃ ለመሰብሰብ የተለያዩ አሰራሮችን ዘርግቶ ወደ ተግባር መግባቱ ይታወቃል
የቢሮው የህግ ተገዢነት ዘርፍ የበጀት አመቱን የሩብ አመት ዕቅድ አፈፃፀሙን ዛሬ ከዳይሬክተሮች ፣ ከቅርንጫፎች ስራ አስኪያጆችና ከስራ ሂደቶች ጋር ከህግ ተገዢነት ዘርፍ አንፃር ገቢን በላቀ ደረጃ የታቀደውን ለመሰብሰብ የተሰሩ ስራዎችን በጥንካሬና በክፍተት የተለዩ አፈፃፀሞችን በመገምገም በቀጣይ የሚሰሩ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን ይፋ አድርጓል ።
በህግ ተገዢነት ዘርፍ የደረሰኝ ቁጥጥር ፣ የታክስ የኢንተለጀንሲ ስራ፣ የመኪና ላይ ኦፕሬሽን ፣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያዎች አጠቃቀም ፣ የኢንቨስትጌሽን ስራዎች አፈፃፀም ፣ የታክስ ከፋዮች የህግ ተገዢነት ንቃት ማሳደግ ስራዎች በዳይሬክቶሬቶቹ ቀርቦ ሰፊ ግምገማና ውይይት ተደርጓል።
ቢሮው ከተማዋ የምታመነጨውን ኢኮኖሚ በአግባቡና በታክስ ህጉ መሠረት ገቢውን ለመሰብሰብ የሚታዩ ችግሮችንና የአሰራር ክፍተቶች ሊታረሙና የመፍትሔ አቅጣጫ ሊሰጥባቸው በሚያስችል ጉዳዮች ዙሪያ የበጀት አመቱን የሩብ አመት ዕቅድ አፈፃፀም ከዘርፉ ዕቅድ አንፃር ከዳይሬክቶሬቶች ፣ ከስራ አስኪያጆች እና ከስራሂደቶች ጋር ነው የገመገመው ።
ውይይቱን የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የህግ ተገዢነት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ ሚኪያስ ሙሉጌታ ” ከቀረበው ሪፖርት በመነሳት የከተማችንን ገቢ ባቀድነው ልክ እና በላቀ ደረጃ ለመሠብሰብ የታክስ ህግ ተገዢነትና ፍትሐዊ የታክስ አሰባሰብ በየደረጃው ሊረጋገጥ ይገባል ብለዋል ።
ለዚህ ስኬትም የህግ ማስከበር ስራው የራሱ አስተዋፅኦ እንዳለው የገለፁት ሀላፊው በበጀት አመቱ ሩብ አመት የታቀደው ዕቅድ አፈፃፀም በየደረጃው በተቀመጠ ጊዜ ሰሌዳ እየተገመገመ የመጣ ይሁን እንጅ አሁንም ሰፊ የሆኑ ክፍተቶች ማለትም የደረሰኝ አለመቁረጥና ቁጥጥር ፣በሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ማሽን ደረሰኝ አለመቁረጥ ፣ ሀሰተኛ ደረሰኝ መጠቀም ፣ አንደር ኢንቮይስ መጠቀምና የመሳሰሉት ትልቅ ተግዳሮቶች ስለሆኑ እነዚህን ችግሮች ለማረምና ለማስተካከል ችግሮቹ ባለቤት ኖሯቸው ሊታረሙና ተጠያቂነትም በማስፈን ቀጣይ የአሰራር አቅጣጫ ሊቀመጥባቸው እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል ።
ያልተሻገርናቸውን ችግሮች ለመውጣት እንዲቻል በታክስ ህግ ተገዢነት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች ላይ በጥልቀት በመወያየት ፣ በችግሮቹ ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ፣ በቀጣይ አሰራርንና ተጠያቂነት በያዘ መልኩ ወጥነት ያለው የህግ ማስከበር ስራዎችን በማከናወን የታክስ ህግ ተገዢነት ደረጃን ማሻሻልና የከተማዋን የላቀ_የገቢ_ዕቅድ ማሳካት እንደሚገባም አመላክተዋል ።
የዘርፉ አመራሮች ፣ በየደረጃ ያላችሁ የስራ መሪዎችና ፈፃሚዎች የመድረኩን ዐላማን በሚገባ ተገንዝቦ ወደራስ በመውሰድ ለመፍትሔው የራስን ሚና መወጣት ፣ ተጠያቂነት ማስፈን እንደሚገባም አብራርተዋል።
በመጨረሻም በተነሱ ችግሮችና የአሰራር ክፍተቶች ዙሪያ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የታክስ ህግ ተገዢነት ስራዎችን እውን ለማድረግና የሚጠበቀውን ታክስ ( ገቢ ) በአግባቡ ለመሰብሰብ እንዲቻል ግብር ከፋዮችን ማስተማር ግንዛቤ ማሳደግ ፣ ፍትሐዊ የንግድና የግብር ስርዐትን ማስፈን ፣ ከታክስ ህጉ በተቃራኒ የሚሰሩትን በመለየት አስተማሪ እርምጃዎችን መውሰድ ፣ ተጠያቂነት ማስፈን ፣ የህግ ተገዢነትን ማሳደግ የቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫና በጥብቅ ዲሲፒሊን የሚመራ መሆኑ ተገልጿል
የዘርፉ የሩብ አመት ዕቅድ አፈፃፀም አበረታች ውጤቶች ቢታዩበትም በቀጣይ የታክስ ኢንተለጀንሲ ፣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያዎች ( ማሽን ) አጠቃቀም ፣ የታክስ ( ግብር ) ከፋዮች የህግ ተገዢነት ደረጃና ስልጠናን ፣ የደረሰኝ ግብይት ቁጥጥርን እና በአዲስ መልክ የተጀመረውን በመዲናዋ በሁሉም አቅጣጫዎች የመኪና ላይ የደረሰኝ ቁጥጥር ተግባራቶች ከመደበኛው አሰራር ውጪም ቁጥጥሩ ሊጠናከር እንደሚገባም በሀላፊው ተመላክቷል
ዘርፉ የቀጣይ የሁለተኛ ሩብ አመት ዕቅድ የሚተገበሩ ዋና ዋና የስራ አቅጣጫዎችን በትኩረት እንዲከናወኑ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል
በውይይቱ ዘርፉን ከዋናው ቢሮ ጀምሮ የሚመሩ ሀላፊዎች ፣ ዳይሬክቶሬቶች እና የቅርንጫፍ የዘርፉ ስራ አስኪያጆችና ስራ ሂደት መሪዎች ተሳትፈዋል ።