የቢሮው የታክስ ዘርፍ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የገቢ እቅድ አፈፃፀም ግምገማ በማካሄድ የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎቹን አስቀመጠ ።

ጥቅምት 5 / 2018 ዓ.ም : አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ

የቢሮው የታክስ ዘርፍ በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያ ሩብ ዓመት አቅዶ ያከናወናቸውን ቁልፍ እና አበይት ተግባራት አፈፃፀሙን ገምግሟል ።

የግምገማውን መድረክ የከፈቱት በቢሮው የታክስ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ወ/ ሮ ወርቅነሽ ሰቦቃ ግምገማው በዕቅድ አፈፃፀሙ የታዩትን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ፣ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይ ያመላከተ እንደሆነ አብራርተዋል ።

መረጃን የማጥራት ስራን ማጠናቀቅ ፣ የጠራና የተደራጀ መረጃን ማጠናከር ፣ የገበያ ዋጋ ጥናትን ያማከለ የኦዲት ውሳኔ ጥራትና ሽፋንን ማሳደግ ፣ የሚወሰኑ ውሳኔዎችን ወደ ገንዘብ መቀየር ፣ የውዝፍ ዕዳን መረጃ በአግባቡ መያዝና መጠቀም እንደሚገባ ሃላፊዋ አሳስበዋል ።

በቀጣይ በአዲሱ የግብር አዋጅ መሰረት ግብር ከፋዮችን በመለየት ቫት መመዝገብ ያለባቸውን የማስገባት ፣ ኢ_ፊሊንግና ኢ_ፔመንትን ማጠናከር ፣ የኤክሳይዝ ታክስ መረጃን ማጠናከር ፣ የፕሪ ኦዲት ስራን ማስፋት ፣ ከህግ ተገዥነት ጋር በቅንጅት መስራት እንዲሁም የግብር ከፋይ መረጃን በአግባቡ መለየትና ማደራጀት እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

በሁሉም ቅርንጫፎች እና ወረዳዎች እንደዘርፍ የሚወርዱ አሰራሮችን በወጥነት የመተግበር ስራ በመስራት እና የስራ ስነምግባርን የተላበሰ የአመራር ሚናን በማሳደግ እንደ ገቢ ሰብሳቢ ቢሮ አመራር የሚጠበቀውን ግዴታ በተሻሻለ መልኩ መወጣት እንደሚገባ ወ/ ሮ ወርቅነሽ አሳስበዋል ።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ላይ የሚመለከታቸው የቢሮው ዳይሬክቶሬቶች ፣ የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጆችና የወረዳ ስራ አስተባባሪዎች እንዲሁም ስራ ሂደት አስተባባሪዎች ተሳትፈዋል ።

በግምገማዊ ውይይቱ ላይ ለተነሱ ሀሳቦች ምላሽና ማብራሪያ ከዘርፉ ሀላፊ እና ዳይሬክቶሬቶች ተሰጥቶበታል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *