ህዳር 3 ቀን 2018ዓ.ም ፣ አዲስ አበባ፣ ገቢዎች ቢሮ
ይህ የተገለጸው በዛሬው ዕለት የቢሮው የሞደርናይዜሽንና የፅ/ቤት ዘርፎች የበጀት ዓመቱን የ4 ወራት ዕቅድ አፈፃፀሞችን ከቅርንጫፍ የዘርፉ አመራሮች ጋር በገመገሙበት መድረክ ነው፡፡
በመድረኩ የቢሮው የፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አዳነ ሱሌ በየደረጃው ያለው አመራር ስራዎችን በአግባቡ በመምራት ውጤት ከማስመዝገብ አኳያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
በተለይም ከአገልግሎት አሰጣጥና ከመልካም አስተዳደር ችግሮች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎች ለመቅረፍ በቢሮው የወረዱ አሰራሮችን በአግባቡ መተግባርና ስራዎችን በቅርበት መምራት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የሰው ኃይል ስምሪትን በፍትሃዊነት መምራት፣ የስራ ሰዓትን በአግባቡ ለአገልግሎት አሰጣጥ መዋልና የዲሲፒሊን ግድፈቶችን ለማረም የሚያስችል ጠንካራ የተጠያቂነት አሰራር ወደ ተግባር ማሸጋገር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩልም ተቋማትን ለተገልጋዮችም ሆነ ለሰራተኞች ምቹ እንዲሆኑ ማድረግና የግልፀኝነት አሰራሮችን እውን ለማድረግ የሪፎርም ተግባራት በአግባቡ ማስተግባር ከሁሉም የዘርፉ አመራሮች የሚጠበቅ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የሞደርናይዜሽን ዘርፍ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ አብዱራማን በበኩላቸው የዘርፉ አመራር በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎቸን ሙሉ በሙሉ መቅረፍ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
አመራሩ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶችን ስትራቴጂክ በመሆኑ መምራት እንደሚጠበቅበት በማንሳት በዚህ ረገድ የተዘረጉ አሰራሮችን ሳይሸራረፉ ወደ ተግባር በማሸጋገር መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የወረፋ ማስጠበቂያ ማሽኖችን በአግባቡ መጠቀም፣ የኢ ፋይሊንግ እና የኢ ፔይመንት አሰራሮችን በማጠናከር የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ማረም የሚገባ እንደሆነም አንስተዋል፡፡
የወረዳዎች አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻልም አገልግሎት አሰጣጡን በቅርበት ከመምራት ጀምሮ ምቹ ሁኔታዎች በመፍጠር ላይ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
