በቴክኖሎጂ የታገዘ የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉ በፊት ከሚደርስባቸው ማጭበርበር እንደታደጋቸው በመርካቶ ያነጋገርናቸው ግብር ከፋዮች አሳወቁ ።

ነሐሴ 12 / 2017 ዓ / ም የአዲስ አበባ፣ ገቢዎች ቢሮ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የቁጥጥር ስራው በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በማድረግ ወደ ተግባር ማሸጋገሩ ይታወቃል ።

የኮሙንኬሽን የዝግጅት ክፍላችን በመርካቶ አካባቢ ዛሬም በመዘዋወር ቢሮው ወደ ተግባር ባሸጋገረው በቴክኖሎጂ የታገዘ የቁጥጥር ስርዓት ላይ ያለውን ሂደት የታክስ ( ግብር ) ከፋዮች አስተያየት ቅኝት አድርጓል ፡፡

በመርካቶ ወረዳ 08 በብሎክ 04 በእንጨት ስራዎች የተሰማሩት አቶ ታደለ ሁበና ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት ” ግብር ሰብሳቢውንና ግብር ከፋዩን ( የንግዱን ማህበረሰብ ) በግልፀኝነት ያገናኘ አሰራር በመሆኑና ከዚህ በፊት ከገቢ ቢሮ ነው የመጣነው የሚሉ አጭበርባሪዎችን የገታ አሰራር በመሆኑ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል

ዩኒፎርሙ ተቋሙንና ግብር ከፋይ ነጋዴውን ግልፅ ለግልፅ ለአንድ ዐላማ ያገናኘን በመሆኑ ይበረታታልም ሲሉ ገልፀዋል ።

በመርካቶ በብሎክ 02 በተዘጋጁ አልባሳት ንግድ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ትዕዛዙ ምስገና በበኩላቸው በፈገግታ ተቀብለውን እንደገለፁት ” አሁን የተጀመረው አሰራር ይለያል በኛም በንግዱ ዘርፍ ውስጥ ያለንን ግብር ከፋዮች ማን በህጋዊ መንገድ በደረሰኝ ይሰራል ፣ ማን አይሰራም ” የሚለው የሚለይበትና ፍትሀዊ የንግድና የታክስ ስርዐት እንዲሰፍን በማድረጉ ተጠናክሮ በሁሉም አካባቢ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል

የበፊቶቹ ገቢ ሳይሆን ከገቢ ነው የመጣነው በማለት በማዋከብ ይበዘብዙን ነበር ያሉት አቶ ትዕዛዙ ቢሮው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ አዳዲስ አሰራሮችን ወደ ተግባር ማሸጋገሩ ገቢው በወቅቱና በአግባቡ እንዲሰበሰብ ያስችላል ሲሉ ገልፀውልናል ።

በሌላ መልኩ በመርካቶ በስኬት የገበያ ማዕከል በኣሌክትሮኒክስ የንግድ ዘርፍ ተሰማርታ ያገኘናት ወጣት አሚና አህመድ በበኩላ ቀደም ብሎ ቆይታ ያደረጉንን ነጋዴዎች ሀሳብ በመጋራት ” የሚገርም ነው ሲመጡ ቀጥታ ማዋከብ ፣ ማስፈራራትና ይህን አርጉ ነው የሚሉት በማለት ወደ ኃላ ትውስታዋን አጫውታናለች ።

ወጣት አሚና መርካቶ ብዙ የንግድ እንቅስቃሴ ቀን በቀን የሚካሄድበት ፣ የአገሪቱ ትልቁ የመገበያያ ስፍራ ስለሆነ በግልፅ ቁጥጥር መደረጉና ተቆጣጣሪዎችን የምንለይበት እና የምንጠይቅበት አሰራር መዘርጋቱ ለግብር ሰብሳቢው ተቋም የነበረንን ግምታዊ አመለካከት የቀየረ ነው ፣ በመሆኑም ጥቅሙ ለሁላችንም ነው ብላለች ።

ከምንም በላይ በቢሮው ስም የሚያጭበረብሩ ወንጀለኞችን ለመከላከልና ለማጋለጥ የሚያስችል መሆኑን ያነጋገርናቸው ግብር ከፋዮች በአንድ ሀሳብ ይስማማሉ ።

የመጡትንም ተቆጣጣሪዎች የባርኮድ የተካተተበት መታወቂያ በመያዛቸው በእጅ ስልካችን ስካን በማድረግ ማንነታቸውን በቀላሉ በመለየት የቢሮው ትክክለኛ የቁጥጥር ባለሙያዎች መሆናቸውን ለመለየት አሰችሎናል ሲሉ ይደመጣሉ ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *