ነሐሴ 14 / 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በበጀት አመቱ የታቀደውን የከተማዋን ገቢ በአግባቡ ለመሠብሰብ አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን ወደ ተግባር አስገብቶ እየሰራ ይገኛል ።
ፍትሀዊ የሆነ የታክስ ( ግብር ) አሰባሰብ ስርዓት በከተማዋ ማስፈንና ይበልጥም የሚሰበሰበው ገቢ ከሌብነትና ብልሹ አሰራር የፀዳ እንዲሆን በህግ ተገዢነት ዘርፍ አሰራርን በመፈተሽ በማስተካከልና ተጠያቂነት በማስፈን ጭምር እየተሰራ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል ።
የቢሮው የህግ ተገዢነት ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ሚኪያስ ሙሉጌታ ከዝግጅት ክፍላችንና ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይት እንደገለፁት ” ተቋሙ የገቢ አሰባሰብ ስርዐቱን ፍትሀዊ ለማድረግ በሚሰራበት ወቅት የሚያጋጥሙትን የህግ ተገዢነት ክፍተት( ተግዳሮቶች ) ለማስቸካከል አሰራሮችን ዘርግቶ ወደ ተግባር ገብቷል ብለዋል ።
በገቢ አሰባሰባችን ከአሰራር ፣ ከአደረጃጀት እና ከሰው ሀይል አንፃር ያሉ ማነቆዎች በጥናት እንዲፈቱና መፍትሔ እንዲቀመጥላቸው መደረጉን ያብራሩት ሀላፊው በዋነኛነት የታክስ ህግ ተገዢነት ማክበርና ማስከበር በመሆኑ ይህም ሲሆን ፍትሀዊነት ያለው የታክስ ( ግብር ) አሰባሰብ ስርዐትና የሌብነትና ብልሹ አሰራር መንገዶች ይዘጋሉ ሲሉ ገልፀዋል
ከሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎች ( የደረሰኝ ማሽን ) አጠቃቀም ፣ከመስክ የቁጥጥር ሰራተኞቻችን አንፃር የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚያርም አሰራር ዘርግተን ወደ ተግባር በመግባታችን ውጤት እያገኘንበት ነው ብለዋል ።
የመስክ ተቆጣጣሪ ሰራተኞቻችን በቁጥጥር ሲሄዱ ከገቢ ቢሮ መምጣቱን የሚያረጋግጥ ለእያንዳንዱ ሰራተኛ መለያ ኮድ ያለው በዲጂታል መታወቂያ መያዛቸው ፣ከዩኒፎርሙ በተጨማሪ ግልፀኝነትን ስለሚያረጋግጥ በቁጥጥር ጊዜ ግብር ከፋዩ የሚያነሷቸው በአስመሳዮች መጭበርበርን ጥያቄዎችን የፈታ መሆኑን አሳስበዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ ማንኛውንም ግብይት በደረሰኝ መፈፀም እንዳለበት ፣ ሸማቹም ማህበረሰብ ደረሰኝ ጠይቆ መቀበል የተከለከለ ከሆነ በቀላሉ የቁጥጥር ሰራተኞቻችን ለይተው የሚያጋጥማቸውን ችግር እንዲፈቱላቸው ያስችላል ሲሉ አቶ ሚኪያስ አብራርተዋል።
በቁጥጥር ወቅት ግብር ከፋዩ ተረጋግቶ ስራውን እንዲሰራ ከብልሹ አሰራር ለመጠበቅ ፣ ከአጭበርባሪ ለመለየትና በቀላሉ መታወቂያቸውን አይቶ እስካን አድርጎ መለየት የሚችልቀት አሰራርም እንደሆነ ተጠቁሟል።
ዋናው ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ በትክክል የሚቆጣጠረውን አካል ለይቶ እራሱ ከአጭበርባሪዎች እንዲጠበቁ አድርጓል ያሉት አቶ ሚኪያስ ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ደረሰኝ መቁረጥና በደረሰኝ መገበያየት እየጨመረ መምጣቱን በሳምንቱ የግምገማ ሪፖርታችን ለማወቅ ችለናል ብለዋል ።
የህግ ማስከበር ስራ በመርካቶ ብቻ ሳይሆን ትልልቅ ግብይት ባላቸው የስራ መሥክና ብሎኮች በሁሉም ገቢ ሰብሳቢ ቅርንጫፍ ባሉበት ክፍለ ከተሞች እየተሰራ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ገልፀዋል ፣ ህግን ማስተማር ፣ መደገፍ ይህን የሚተላለፍ ደሞ ተጠያቂ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑንም አመላክተዋል
በመርካቶ ዙሪያና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ላይ በዪኒፎርም ቢሰራም በሁሉም ክፍለ ከተሞቻችን የህግ ማስከበር ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል ።
እንደ ቢሮ አሰራሮችን በቴክኖሎጂ በማገዝ ወደ ስራ የገባንባቸው በርካታ ስራዎች መኖራቸውንም ሀላፊው ገልፀዋል
ከመታወቂያ ባሻገር ፣ በቀጣይም ይፋ የሚደረጉ የቴክኖሎጂ አሰራሮች እንዳሉ የጠቆሙት ሀላፊው ፣ የአገልግሎት አሰጣጡን እንቅስቃሴ ለመከታተልና ለማረም እንዲያስችል ከማዕከል የካሜራ ሰርቨይ ቴክኖሎጂዎች እውን መሆኑንና የታክስ ፍትሀዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል ።
ገቢ ለመሠብሰብ ሁሉም አካላት ርብርብ ይፈልጋል ፣ የህግ ተገዢነት ተረጋግጦ ፍትሀዊ የገቢ አሰባሰብ እንዲፈጠር ሁሉም ግብር ከፋዮች ዘመናዊነት የተላበሰ የደረሰኝ ግብይት ማድረግ ግዴታ መሆኑን አውቆ መሥራት እንደለበትም ተገልጿል ።
ሸማቹ ማህበረሰብ በሚገዛው ዕቃ ላይ የከፈለበት በመሆኑ ደረሰኝ መቀበልና የመንግስት ገቢ በአግባቡ እንዲሰበሰብ ደረሰኝ የመጠየቅና የመቀበል ባህሉን ማዳበርና ማጠናከር አለበት ብለዋል
የከተማዋ እና የህዝቡ የመልማት ፍላጎት የሚረጋገጠው ከተማዋ በውስጥ አቅሟ የምትሰበስበው ገቢ በመሆኑ ገቢው በአግባቡ እንዲሰበሰብና የ2018 የገቢ ዕቅድ እንዲሳካ ሁሉም የጋራ ርብርብ በማድረግ የታክስ ህግ ተገዢነት እንዲሰፍ መሥራት እንደሚገባ ሀላፊው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።