ጥቅምት 22 ቀን 2018ዓ.ም፣ አዲስ አበባ ፣ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በማዕከል፣ በሁሉም ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶችና ወረዳዎች ከሚገኙ አመራሮችና ፈፃሚዎች ጋር በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋሉ ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል የውይይት መድረክ በማዕከልና በሁሉም ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶቹ አካሄደ፡፡
በውይይት መድረኩ የቢሮው ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ ተቋሙ ፍትሃዊ የግብር አሰባሰብ ስርዓት በማስፈን ተልዕኮውን በአግባቡ ለመወጣት አዳዲስ አሰራሮችንና አደረጃጀቶች በጥናት በመለየት እንዲሁም በውስጥ አቅምና ከተባባሪ አካላት ጋር በመቀናጀት ቴክኖሎጂዎችን በማልማት ወደ ተግባር ለማሸጋገር ጥረት አደርጓል ብለዋል፡፡
በዚህም ለከተማዋ ልማት የሚውል ገቢን በብቃት ከመሰብሰብ እንዲሁም የግብር ከፋዩን የህግ ተገዢነት በማሻሻል ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች ለማስመዝገብ ተችሏል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ለግብር ከፋዮች የሚሰጥ አገልግሎትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል ያሉት አቶ ቢኒያም አሁንም ግን ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በግብር ከፋዩ ዘንድ የሚነሱ ሰፊ ቅሬታዎች በመኖራቸው ገልጸዋል፡፡
ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎች ምንጮች ከፈፃሚ ጀምሮ በየደረጃው ያለው አመራር ኃላፊነቱን በአግባቡ ካለመወጣት፣ ውሳኔዎች በየደረጃው ሊወሰኑ ሲገባቸው ባለመወሰን፣ ቅሬታዎች በማድመጥ ተገቢ ምላሽ ባለመስጠት፣ ባለጉዳዮችን አለአግባብ በማመላለስ የሚመነጩ ናቸው ብለዋል፡፡
በመሆኑም በተቋሙ በአገልግሎት አሰጣጥ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የግድ ነው ያሉት ኃላፊው ለዚህ ሁሉም ፈፃሚና አመራር ኃላፊነት እንዳለበት በመረዳት እራሱን ለመለወጥ ዝግጁ ማድረግ ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም በተቋሙ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለመቅረፍ አመራሩ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የገለፁት ኃላፊው ለዚህም የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ስትራቴጂ በመንደፍ ወደ ተግባር እያሸጋገረ ይገኛልም ብለዋል፡፡
ይሁንና በቅርንጫፍ ፅ/ቤትም ሆነ በወረዳ ደረጃ በስራ ክፍሎች መካከል ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር፣ ለግብር ከፋዮች ተገቢውን ክብር በመስጠት አገልግሎት መስጠት፣ የተጠያቂነት አሰራርን ማጠናከር፣ በቢሮው የለሙ ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ ወደ ተግባር ማሸጋገር ይገባልም ብለዋል፡፡
