ታህሳስ 4 / 2018 ዓ . ም : አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ አስተዳደሩ ገቢዎች ቢሮ ፍትሃዊ የግብር አሰባሰብ ስርዓት በማስፈን በግብር ከፋዮች የሚነሱ የታክስ ውሳኔ ቅሬታዎችን እየፈታ መሆኑ ተገልጿል ።
ይህ የተገለፀው በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ባለፉት 6 ወራት ከቅሬታ አቀራረብና አፈታት ጋር በተያያዘ ያከናወናቸው ተግባራት ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው።
በቢሮው የታክስ ውሳኔ ቅሬታ አጣሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ ደጌ በበጀት ዓመቱ 6 ወራት ለቢሮ ከቀረቡት 13 ሺህ 643 የታክስ ውሳኔ ቅሬታዎች መካከል11 ሺህ 892 ወይም 89 በመቶ ምላሽ ተሰጥቷል ብለዋል።
ከዚህ ውስጥም 6,940 ወይም 58 መቶ ውሳኔዎች ግብር ከፋዮች ያቀረቧቸው ቅሬታዎችና መረጃዎች ተቀባይነት በማግኘታቸው ውሳኔዎቹ በማሻሻል የተወሰኑ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
እነዚህም የታክስ ቅሬታዎች ከታክስ ኦዲት ፣ ከኢንቨስትጌሽን ኦዲት ፣ ከቀን ገቢ ግምት ፣ ከሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ቁጥጥር እና ከታክስ አወሳሰን በተያያዘ የቀረቡ ቅሬታዎች መሆናቸውን አቶ ኤርምያስ ጠቁመዋል ።
በሌላ በኩልም ከቢሮው ባለሙያዎች ጋር ያልተገባ ግንኙነት በመፍጠር የመንግስትን ጥቅም በሚያሳጣ ደረጃ የተወሰኑ ውሳኔዎች በቢሮው በተደራጀ የኦዲት ጥራት አረጋጋጭ የስራ ክፍል ዳግም ኦዲት በማድረግ ውሳኔዎቹ እንዲሻሻል በማድረግ የመንግስትን ጥቅም የማስጠበቅ ተግባር መከናወኑንም አብራርተዋል።
የታክስ ቅጣት ውሳኔዎችን በማንሳትና የግብር ከፋዩን ጥያቄ በመመለስ ግብር ከፋዩ በንግድ ስርዓት ውስጥ እንዲቆይ ከማድረግ አኳያም በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ደግሞ የገለፁት አቶ ንብረት በሪሁን የታክስ ዕዳ አስተዳደር ዳይሬክተር ሲሆኑ በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት የ262 ግብር ከፋዮች ቅጣት ይነሳልኝ አቤቱታ በማድመጥና መረጃዎችን በመመርመር ከ579 ሚሊዮን ብር በላይ ቅጣት ማንሳቱንም አብራርተዋል።
ከዚህም ባሻገር ለ170 ግብር ከፋዮች ከ6-24 ወራት የጊዜ ስምምነት በመስጠትም ተገቢው ድጋፍ መደረጉምንም ጠቁመዋል።
በመጨረሻም ቢሮው ግብር ከፋዮች የታክስ ውሳኔ ቅሬታ ካላቸው የሚፈታበት ስርዓት በመዘርጋት እየፈታ መሆኑን በመገንዘብ በተዘረጋው አሰራር ብቻ በመጠቅም ቅሬታዎቻቸውን እንዲያቀርቡም ጥሪ ቀርቧል።
ውጤታማ የገቢ አባሰብ ለአዲስ አበባ ብልጽግና
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የግብር ከፋዮችን ቅሬታ በማድመጥ 58 በመቶ የውሳኔ ማሻሻያ በማድረግ ተገቢውን ምላሽ እየሰጠና ከ579 ሚሊዮን ብር በላይ ቅጣት በማንሳት ለግብር ከፋዩ እገዛ ማድረጉ ተገለፀ።
