ቢሮው የ2018 ግማሽ በጀት ዓመት የተቋማትና የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራዎች አፈፃፀም ላይ ውይይት አካሄደ፡፡

ጥር 21 / 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2018 ግማሽ በጀት ዓመት ያቀደውን ፍትሃዊ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት በመዘርጋት የከተማዋ የልማት ወጪ በአግባቡ ለመሸፈን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር ሲሰራ ቆይቷል፡፡
በዛሬው ዕለትም ቢሮው በቅንጅታዊ ስራዎች በተለዩ አፈፃፀሞች በተስተዋሉ ክፍተቶች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላቱ ጋር በመገምገም ቀጣይ ኣቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
በመድረኩ የቢሮው የታክስ ጉዳዮች ዘርፍ ም/ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ወርቅነሽ ሰቦቃ ቢሮው በግማሽ በጀት ዓመቱ ከተቋማት ጋር ተቀራርቦ በቅንጅት በመስራት የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ ችሏል ብለዋል፡፡
በተለይም በቅንጅታዊ ስራዎች በተቋሙ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
ከገቢ አሰባሰብ አኳያም ፍትሃዊ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት ለመዘርጋት፣ የገቢ መሰረት ለማስፋት ፣ አዳዲስ የገቢ ምንጮችን በጥናት ለመለየትና ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስችሉ ተግባራት በጋራ ለማከናወን መቻሉን ያነሱት ወ/ሮ ወርቅነሽ በዚህም በከተማ ደረጃ ከታቀደው ገቢ ከ92.07 በመቶ እንዲሁም በቢሮው ከታቀደው ገቢ 99.12 በመቶ ለማሳካት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ይሁንና በግማሽ በጀት ዓመቱ ከቅንጅታዊ ስራዎች ትግበራም ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ክፍተቶች እንደነበሩም በማንሳት በቀሪዎቹ የበጀት ዓመቱ ወራት ክፍተቶችን በመለየት ለመቅረፍ በጋራ መረባረብ እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡
በመድረኩ ተሳታፊ የሆኑ ተቋማትም ቢሮው የከተማዋ ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ገቢ በብቃት ለመሰብሰብ፣ የግብር አሰባሰብ ስርዓቱን ለማዘመን፣ የስነ ምግባርና የሌብንት ችግሮችን ለመቅረፍ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
አክለውም በከተማዋ ከሴክተር ተቋማት ለመሰብሰብ የታቀደ ገቢ በተሟላ ደረጃ እንዲሳካ ሚናቸውን በአግባቡ እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ የቅንጅታዊ ስራዎች የግማሽ በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በመድረኩ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከቢሮው አመራሮች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *