ኢዲስ አበባ፣ ጥር 22 ቀን 2018ዓ.ም ፣ አዲስ አበባ፣ ገቢዎች ቢሮ
ይህ የተገለጸው ቢሮው በማዕከል ደረጃ ከተደራጁ የመማክርት ጉባኤ አባላት ጋር ባለፉት 6 ወራት በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በሌብነትና ብልሹ አሰራር ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ለማረም በተከናወኑ ተግባራት ላይ ውይይት ባካሄደበት መድረኩ ነው፡፡
በመድረኩ የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ም/ቤት ፕሩዝዳትና የመማክርት ጉባኤው ሰብሳቢ ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ ቢሮው ባለፉት 6 ወራት የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር እንዲሁም መድረኮችን በማመቻቸት ከግብር ከፋዮች ጋር ተቀራርቦ በመስራት የተሻሉ አፈፃፀሞችን ለማስመዝገብ ችሏል ብለዋል፡፡
በተለይም በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋሉ ችግሮች ለመቅረፍ የመማክርት ጉባኤው መደራጀቱ ፋዳው የላቀ መሆኑን ያነሱት ወ/ሮ ዘሃራ ከዚህ አኳያ የመማክርት ጉባኤ አባላቱ ተልዕኳቸውን በአግባቡ በመገንዘብ ለመወጣት መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
አክለውም ግብር ከፋዮች መብትና ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲገነዘቡ ለማስቻልም በየቅርንጫፉ የተደራጁ የመማክርት ጉባኤዎች ወደ ተግባር መግባት አለባቸውም ብለዋል፡፡
የመማክርት ጉባኤው የግብር ከፋዮች ድምፅ በመሆን ግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤቱና ግብር ከፋዩን ይበልጥ የማቀራረብ፣ ችግሮች በውይይትና በጋራ የሚፈቱበት ስልት የመቀየስና አዳዲስ ሃሳቦች የማፍለቅ ሚናውን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች በመቅረፍ ቢሮው የግብር ከፋዮች እርካታ ለማሻሻል፣ የቅሬታ አፈታት ስርዓቶችን ለማጠናከር የሚያከናውናቸው ተግባራት ውጤታማነት ለማላቅ ተገቢውን እገዛ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
በቢሮው የሞደርናይዜሽን ም/ቢሮ ኃላፊና የመማክርት ጉባኤው ም/ሰብሳቢ አቶ መሀመድ አብዱራማን በበኩላቸው ተቋሙ የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ ለመወጣት በግማሽ በጀት ዓመቱ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል፡፡
በተለይም ለሌብነትና ብልሹ አሰራር በር የከፈቱ ጉዳዮች በመለየት 24 በሚደርሱ አዳዲስ አሰራሮችንና አደረጃጀቶችን በጥናት በመለየትና ወደ ተግባር በማሸጋገር እንዲሁም በቴክኖሎጂ ልማት ውጤታማ ተግባራት ለማከናወን ችሏል ብለዋል፡፡
በሰው ሀብት ልማት ረገድም የባለሙያዎች የአገልጋይነት ስብእና ለማጎልበት የሚያስችሉ የአመለካከትና የክህሎት ግንባታ ስራዎች በማከናወን ተቋማዊ አቅም ለማጎልበት መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
በግማሽ በጀት ዓመቱ የተጠያቂነት አሰራርን ከማጠናከር አኳያም 282 የሚደርሱ አመራሮችና ባለሙያዎች አገልግሎት በአግባቡ ካለመስጠት ጀምሮ በሌብነትና በብልሹ አሰራሮች ውስጥ ገብተው በመገኘታቸው ተጠያቂ መደረጋቸውን አንስተዋል፡፡
በመድረኩ ተሳታፊ የሆኑ የመማክርት ጉባኤው አባላት በበኩላቸው ቢሮው በግማሽ በጀት ዓመቱ የመማክርት ጉባኤውን በማደራጀት ወደ ተግባር ማሸጋገሩ ለውጥ ፈላጊ መሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በግማሽ በጀት ዓመቱም አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለመቅረፍ የግልፀኝነትና የተጠያቂነት አሰራር ለማጠናከር የተከናወኑ ተግባራት በቀጣይም ሊጠናከሩ የሚገባቸው መሆናቸው ተናግረዋል፡፡
የመማክርት ጉባኤውን ውጤታማነት ለጎልበትም በየቅርንጫፉ ፅ/ቤቶች የተደራጁ አደረጃጀቱን አቅም የማጠናከር የቢሮውና መሰል ግብአት ችግሮች የመቅረፍ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ብለዋል፡፡
በዕለቱ የቢሮው የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የመልካም አስተዳደርና የሌብነትና ብልሹ አሰራር የ6 ወር አፈፃፀም ሪፖርት በቢሮው የሞደርናይዜሽን ዘርፍ ም/ቢሮ ኃላፊ በአቶ መሀመድ አብዱራማን የቀረበ ሲሆን በተሳታፊዎች ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
በመጨረሻም የቢሮው የመማክርት ጉባኤ አባላት በግማሽ በጀት ዓመቱ ወደ ተግባር የተሸጋገሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጉብኝት አካሄደዋል፡፡
ቢሮው የግብር ከፋዮች የመማክርት ጉባኤ በማደራጀት ወደ ተግባር ማስገባቱ ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት ያለው ቁርጠኛነት ማሳያ ነው ሲሉ የመማክርት ጉባኤ አባላት ገለፁ፡፡
