የካቲት 15 ቀን 2018ዓ.ም ፣ አዲስ አበባ፣ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የግብር ስወራን ለመከላከልና የንግድ ሥርዓቱን ፍትሀዊነት ለማረጋገጥና የህግ የበላይነትን ለማስከበር በተከናወነ የተጠና፣ የተቀናጀና ድንገተኛ ኦፕሬሽን በ5 የሱፍ ልብስ ንግድ ድርጅቶች ደረሰኝ ሳይቆርጡ ግብይት ሲፈጽሙ የተገኙ 7 ተጠርጣሪዎችን በህግ ቁጥጥር ስር ማዋሉን አሳወቀ።
ቢሮው የካቲት 14 ቀን 2018ዓ.ም በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ባካሄደው የተጠና የኦፕሬሽን ተግባር በ5 የንግድ ድርጅቶች በድምሩ 7 ግለሰቦች በሕግ የተጣለባቸውን የደረሰኝ አጠቃቀም ግዴታ ባለመወጣት ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል ብሏል።
በዚህም ከድርጊቱ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸው የንግድ ስራዎቹ ባለቤቶችና ሽያጩን ያለደረሰኝ ሲያከናውኑ የነበሩ ሰራተኞች የመንግስትን ግብር ለመሰወር ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ ተገኝተው በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸውን አሳውቋል፡፡
ቢሮው የኦፕሬሽን ተግባሩ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ማካሄዱን የተገለፀ ሲሆን በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች የመንግሰትን ጥቅም ለማሳጣት ከታክስ አስተዳደር አዋጅ በተፃረረ መልኩ ያለደረሰኝ ሽያጭ በመፈፀም ወንጀል ተጠርጥረው በአሁኑ ወቅት ጉዳያቸው በፖሊስ ተይዞ ለፍርድ የሚቀርቡ ይሆናል ብሏል፡፡
በቀጣይ ቀናትም ቢሮው የኦፕሬሽን ተግባሩን በሌሎችም ዘርፎች አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያሳወቀ ሲሆን የንግዱ ማህበረሰብ ግብይቶችን በደረሰኝ ብቻ እንዲፈፅም ህብረተሰቡም በ7075 ነፃ የስልክ መስመር በመጠቀም መሰል ወንጀሎችን እንዲያጋልጥ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ቢሮው ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በጎማ፣ በኤሌክትሮኒክስና በኮንስትራክሽ፣ በስጋ ቤትና በግንባታ ዕቃዎች ንግድ ላይ በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ ባካሄደውኦፕሬሽን 67 ተጠርጣሪዎች ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ በመያዝ በህግ ቁጥጥር ስር ማዋሉ የሚታወስነው፡፡
በመዲናዋ በሱፍ ልብስ ንግድ ስራ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ የተገኙ 7 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡
