ህዳር 15 ቀን 2018ዓ.ም ፣ አዲስ አበባ ፣ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ አመራሮችና ሰራተኞች በዛሬው ዕለት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ22ኛ፣ በሀገር አቀፍ ደግሞ ለ21ኛ ጊዜ ‹‹ትውልድን በስነ ምግባር ተቋም በአሰራር›› በሚል መሪ ቃል የፀረ ሙስና ቀንን በፓናል ውይይት አክብረዋል፡፡
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቢሮው ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ ቢሮው ለከተማዋ ልማት የሚውል ገቢን በፍትሃዊነት በመሰብሰብ ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት እያንዳንዱ አመራርና ፈፃሚ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮች በአግባቡ በመረዳት ለመቅረፍ መረባረብ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አንዳድ ግብር ከፋዮችን ምሬት ውስጥ እያስገባ ያለው የሚከፍለው የግብር መጠን አይደለም ያሉት ኃላፊው ዋናው ችግርና የቅሬታ ምንጭ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ግብር ከፋዩ ለሚያቀርበው ጥያቄ አግባብነት ያለውና ጥራቱን የጠበቀ ምላሽ አለመስጠት ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ስለሆነም ከስነ ምግባር ጉድለት የሚመነጩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ማረም የሁሉም አመራርና ፈፃሚ ተቀዳሚ ሚና እንደሆነ በመግለፅ ግብር ከፋዮች ባልተገባ መልኩ ማመላለስ፣ ውሳኔን ማዘግየት፣ ኃላፊነት የጎደለው ምላሽ መስጠት ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከተማችን በጀመረችው ፈጣን ልማትና ዕድገት ልትቀጥል የምትችለው የቢሮው ተገልጋይ የሆነው ግብር ከፋይ በሚከፍለው ግብር መሆኑን ያነሱት አቶ ቢኒያም ለግብር ከፋዮች ተገቢውን ክብር መስጠትና ከግብር ከፋዮች ለሚቀርቧቸው ጥያቄዎች ተገቢ ማጣራት በማድረግ ህጋዊ አሰራር ጠብቆ ፍትሃዊ ውሳኔና ምላሽ በፍጥነት መስጠት ከሁሉም ፈፃሚና አመራር ይጠበቃልም ብለዋል፡፡
በመድረኩ የቢሮው የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተሸመ ሄደታ የስነ ምግባር፣ የሙስና ምንነት፣ ባህሪያት፣ መገለጫዎች፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተፅእኖዎችና መፍትሄዎች፣ በገቢዎች ቢሮ መገለጫዎች ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ሰነድ በማቅረብ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በመጨረሻም በቀረበ ሰነድ ላይ ከተሳታፊዎች ሃሳብና አስተያየት የተሰጠ ሲሆን በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ ከመድረክ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
