በግብር ከፋዮች የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ በተዘጋጀ የ6 ወራት የተከለሰ ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ፡፡

የካቲት 14 ቀን 2018ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፣ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2018 በጀት ዓመት የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር ማሸጋገሩ ይታወቃል፡፡
በዛሬው ዕለት ደግሞ ቢሮው ዕቅዱን በመከለሰ ከ7 ሺህ በላይ ከሆኑ ባለሙያዎችና በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ የቢሮው ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ ቢሮው የከተማዋ ኢኮኖሚ የሚያመነጨው ገቢ በፍትሃዊነት በመሰብሰብ ለከተማ ልማት ለማዋል የሚያስችል የሪፎርም ተግባራት በአሰራር፣ በአደረጃጀት፣ በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ልማት ግንባታ በማከናወን ተጨባጭ ውጤቶች ማስመዝገብ ችሏል ብለዋል፡፡
ይሁንና ቢሮው በገቢ ዘርፉ እያስመዘገበ ያለውን ውጤት በአገልግሎት አሰጣጥና በመልካም አስተዳደር የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ የተሟላ ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡
በቢሮው አብዛኛው አመራርና ባለሙያ ማገልገል ክብር መሆኑን በመረዳት ግብር ከፋዮችን በአግባቡ እያስተናገደ ነው ያሉት ኃላፊው ይሁንና ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም ከቅንነት መጓደልና ከብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ ግብር ከፋዮችን የሚያማርሩ ባለሙያዎች እንዳሉም ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም ቢሮው በግብር ከፋዮች የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ምንጭ በአግባቡ በመለየትና መፍትሄዎችን በማስቀመጥ የግብር ከፋዮችን እርካታ ለማረጋገጥ የሚያስችል የቀጣይ 5 ወራት የተከለሰ የመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር አሸጋግሯል ብለዋል፡፡
የቢሮው የሞደርናይዜሽን ዘርፍ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ አብዱራማን የተከለሰውን ዕቅድ ያቀረቡ ሲሆን ሰፊ ውይይትም ተካሂዷ፡፡
በዕለቱ በ17ቱም ቅርንጫፍ ፅ/ቤት በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች ቢሮው የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ያዘጋጀውን የተከለሰ ዕቅድ በዕለት ተዕለት ስራዎቻቸው ወደ ተግባር በማሸጋገር የተገልጋዮችን እርካታ ለማረጋገጥ ቁርጠኛነታቸውን ገልፀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *