ቢሮው ባለፉት 6 ወራት በሀሰተኛ የተጭበረበረ ደረሰኝ መንግስት ሊያጣ የነበረው ከ422 ሚሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተገለፀ ።
ጥር 18 / 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2017 በጀት ዐመት 6 ወራት በሀሰተኛ ደረሰኝ ግብይት ተጭበርብሮ ያለ አግባብ ሊቀር የነበረ ከ422 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳንና የመንግስትን ጥቅም ማስጠበቅ መቻሉን ገልጿል ።
የቢሮው የህግ ተገዢነት ዘርፍ በየደረጃው ከሚገኙ የቅርንጫፍ የታክስ ሕግ ተገዢነት ዘርፍ አመራሮች ፣ ዳይሬክተሮችና ሰራተኞች ጋር የዘርፉን የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀሙን በጋራ ገምግሞ የቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የሕግ ተገዢነት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚኪያስ ሙሉጌታ እንደገለፁት የመድረኩ ዋነኛ ዓላማ በዘርፉ የ2017 በጀት ዐመት የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ከተቋም የትኩረት አቅጣጫዎች ከተቀመጡ ግቦች በምን ያህል መጠንና ጥራት ለገቢ አሰባሰቡ ስኬት እንደተፈጸሙ በመገምገም የታዩ ጠንካራ ጎኖች ለማፅናት እና ደካማ ጎኖችን በማሻሻል በቀጣይ ቀሪ ወራት የታቀደው ዕቅድ በላቀ ደረጃ እንዲፈጸም አቅጣጫን ማስቀመጥ እንደሆነ ገልጸዋል ።
እንደከተማ የተቀመጠው የገቢ እቅድ ለማሳካት የህግ ተገዢነትን ና የታክስ ህግን በማስፈፀም ረገድ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እና ፈጻሚዎች እየተመዘገቡ የሚገኙ የተሻሉ አፈጻጸሞችን እንደ ግባት በመውሰድ ክፍተት የታየባቸው ስራዎችን በቀጣይ በልዩ ትኩረት አቅዶ ለማስተካከል እንዲሁም በትግልና በውጤት ለመምራት እና በቁርጠኝነት ለመፈጸም እንደሆነ አቶ ሚኪያስ አፅንኦት ሰጥተው ገልፀዋል ።
በ6 ወራት የገቢ ዕቅድ አፈፃፀም በዘርፉ የተገኘ ውጤት ለቀሪ የበጀት ዐመቱ ዕቅድ ስኬት ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ሀላፊው አፈፃፀማችንን በጥልቀት በመገምገም የቀጣዬ አቅጣጫዎች ይቀመጣል ብለዋል ።
ቢሮው ባለፉት 6 ወራት በሀሰተኛ የተጭበረበረ ደረሰኝ መንግስት ሊያጣ የነበረው ከ422 ሚሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ነው ሀላፊው የገለፁት ።
” ሀሰተኛ ደረሰኝ እንዲጣሩ ከቀረቡት አጠቃላይ 18,542 ደረሰኞች 3,301 ሀሰተኛ ሆነው ተገኝተዋል ብለዋል።
ሀሰተኛ ደረሰኞቹ የያዙት 422 ሚሊየን 848 ሺህ 248 ብር በመሆኑ ይህንን ማዳን መቻሉን ፣ ወጪና ያልተገባ ታክስ ያለ አግባብ እንዳይወራረድ መደረጉን አቶ ሚኪያስ በመድረኩ አብራርተዋል።
በቀጣይ የበጀት ዐመቱ ቀሪ ወራት የታክስ ህግ ተገዢነትን ለማስፈንና ገቢን ለማላቅ በውስጥ የሚታዩ የብልሹ አሰራር ፣ የሌብነት አመለካከትና ተግባር ፣ የደረሰኝ አጠቃቀም እና የታክስ ስወራ በትግል በመምራት ግብር ላለመክፈል የሚደረጉ ጥረቶችን በማምከንና የተጠናከረ ኦፕሬሽን ስራዎችን በተጠና መልኩ በመሥራት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በትኩረት እንደሚሰራም አመላክተዋል ።
ከጊዜ ወደ ጊዜ በህገወጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ደረሰኝ የማይቆርጡ ፣ ግብር የሚሰውሩ ፣ በሀሰተኛ ደረሰኝ የሚጠቀሙ ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ የተግባቦት ስራ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች ፣ የውይይት መድረኮች ከመፍጠር ባሻገር ጠበቅ ያለ የህግ እርምጃ በተጨባጭ እየተወሰደ መሆኑን የጠቆሙት ሀላፊው በቀጣይም አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል ።
በአስመጪዎች፣ በአምራቾች ፣ በአከፋፋዮች እንዲሁም ቸርቻሪዎች ላይ የተጀመረው የታክስ ህግ ተገዢነት የማስፈን ተግባር በቀሪ ወራትም እንደሚጠናከር ተጠቁሟል ።
ታክስ ከፋዮ ህብረተሰብ ግብር መክፈል የመልካም ዜጋ መገለጫ መሆኑን በመረዳት ግብራቸውን በህጉ መሰረት በታማኝነትና በወቅቱ አሳውቀው እንዲከፍሉ እና የዘርፉ አመራሮችና ሰራተኞች በ 6 ወራት የታዩ ክፍተቶችን በማሻሻልና ጥንካሬዎች በማፅናት ቢሮ ለመሰብሰብ ያቀደውን የላቀ የገቢ እቅድ ለማሳካት በቀሪ ወራት እንዲረባረቡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።
በመድረኩ የዘርፉን ዕቅድ ዳይሬክተሮችና የተመረጡ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች የ6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በዝርዝር ቀርቦ በተሳታፊዎችሰፊ ውይይት እና መግባባት ተደርጎባቸዋል ።
በሪፖርቱ መነሻነት የታዩትን ጥንካሬዎችን በማጎልበት የታዩ ክፍተቶችን በማረም በቀጣይ ቀሪ ወራት የህግ ተገዢነትን በላቀ ሁኔታ በመፈፀም የገቢ ዕቅዱን ለማሳካት በቁርጠኝነትና በተጠያቂነት ጭምር ዘርፉ እንደሚሰራ በግምገማ በአቅጣጫ ተቀምጧል ።