ቢሮው የበጀት ዓመቱን 6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀሙን በመገምገም ፣ የቀጣይ 6 ወራት የተከለሰ ዕቅዱን ይፋ አደረገ ።
ጥር 15 / 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የበጀት አመቱን የ6 ወራት የገቢ ዕቅድ አፈፃፀሙን በየደረጃው ካሉ አመራሮች ፣ ዳይሬክተሮችና የቡድን መሪዎች ጋር በጋራ ገምግሞ የቀጣይ ቀሪ 6 ወራት የተከለሰ ዕቅድን ይፋ አድርጓል ።
መድረኩን የመሩት የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ሀላፊ አቶ ቢንያም ምክሩ እንደገለፁት ” በበጀት አመቱ የ6 ወራት አፈፃፀምን በመገምገም የታዩ ጥንካሬዎችን በማስቀጠልና ይበልጥ ለገቢ አሰባሰብ የነበሩ ተግዳሮቶችን በመለየት በቀጣይ 6 ወራት የሚከናወኑ የተከለሰ ዕቅድን ወደ ተግባር እናሸጋግራለን ብለዋል ።
የበጀት አመቱን ዕቅድ ለማሳካት በርካታ ተግባራቶች መከናወናቸውን የገለፁት ሀላፊው በ6 ወራት ለተገኘው አፈፃፀም ከዋናው ቢሮ እስከ ታችኛው መዋቅር የተናበበ አሰራርና አቅጣጫዎች ተፈፃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው ፣ የታዩ ጉድለቶች በቀጣይ ቀሪ 6 ወራት ታርመው የታቀደው የገቢ ዕቅድ እንዲሳካ ወደ ተግባር ለመግባት የተከለሰ ዕቅድ መውረዱን ተናግረዋል ።
የበጀት ዓመቱ የገቢ አሰባሰው ውጤታማነት ካለፉት ጊዜያት አኳያ የተሻለ ቢሆንም ከተማዋ ካላት የገቢ አቅም አኳያ በቀጣይ ይበልጥ ማጠናከርና የሚፈለገውን ገቢ በአግባቡ መሠብሠብ ላይ ቁርጠኝነት ይጠይቃል ሲሉ ገልፀዋል
በቀጣይ 6 ወራት ዕቅድ አተገባበር ላይ ከአደረጃጀት ፣ ከሰው ሀይል ሪፎርም፣ ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠርና የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን ፣የተጀመሩ የቁጥጥር ስራዎችን ይበልጥ ማጠናከር ፣ የሌብነት ፣ ብልሹ አሰራርና የታክስ ስወራን መታገል እንዲሁም የህግ ተገዢነትን በማስፈን ታክስን በሚገባ መሠብሰብ ከዕቅዶቹ ዋና ዋናዎቹ መሆኑን ሀላፊው አፅንኦት ሰጥተው ገልፀዋል ።
የበጀት አመቱ 6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በቢሮው የዕቅድ በጀት ዝግጅት ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር በአቶ ጥላሁን ግርማ ቀርቦ በቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች፣ በዳይሬክተሮችና በባለሙያዎች የነበሩ ጥናካሬ ይበልጥም በታዩ ክፍተቶችና ተግዳሮቶች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል ።
በተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ዙሪያ ከመድረኩ በአመራሮችና በየስራ ክፍሎች ሀላፊ ምላሽና አቅጣጫዎች ተሰጥቷል
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቢሮው ዘርፎች ስር ያሉ የቅርንጫፍ የዘርፍ ስራ አስኪያጆች ላይ የተደረገ ምዘና ይፋ ተደርጎ ውይይት ተደርጎበታል፣ በምዘናው ቅርንጫፎች ያሉበትን ደረጃ በመገምገም በቀጣይ ቀሪ ወራት ይበልጥ ተግተው እንዲሰሩ ለማድረግ መሆኑ ተጠቁሟል ።