ባለፉት 6 ወራት ያለደረሰኝ ሽያጭ ላይ በተካሄደ ቁጥጥር በቅጣት ከ297 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተገለፀ፡፡
ጥር 20 ቀን 2017ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፣ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2017 ግማሽ በጀት ዓመት ያለደረሰኝ ሽያጭ ላይ ባካሄደው ቁጥጥር 297 ሚሊዮን 250 ሺህ ብር ከቅጣት መሰብሰቡ ተገልፆል፡፡
በቢሮው የኢንተለጀንስ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ነጋሽ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት ያለደረሰኝ ሽያጮች ለመቆጣጠር ግማሽ በጀት ዓመቱ በትኩረት መስራቱን በመግለፅ በ671 የንግድ ድርጅቶች ላይ በተካሄደ የኢንተለጀንስ ስራ 632 የንግድ ድርጅቶች ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲያከናውኑ በመገኘታቸው አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃዎች ተወሰደዋል ብለዋል፡፡
በዚህም 63 ሚሊዮን 200 ሺህ ብር ለመሰብሰብ ተችሏል ያሉት አቶ ተስፋዬ 839 ተጠርጣሪዎች ላይም ከአስተዳደራዊ ቅጣት ባሻገር የወንጀል ክስ በመመስረት ጉዳያቸው በምርመራ ሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የቢሮው የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ አጠቃቀም ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ልደቱ በበኩላቸው በግማሽ በጀት ዓመቱ ካለደረሰኝ ሽያጭ ጋር በተያያዘ በተከናወነ ክትትልና ቁጥጥር 3 ሺህ 225 የደረጃ ሀ እና ለ ግብር ከፋዮች ላይ ያለደረሰኝ ሽያጭ በማከናወን በተወሰደ አስተዳደራዊ እርምጃ 234 ሚሊዮን 050 ሺህ ብር በቅጣት ገቢ ተሰብስቧል ብለዋል፡፡