ግብር ከፋዩ በእጁ ያለው ማንዋል ደረሰኝ ከየካቲት 2 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት ላይ የማይውል መሆኑን በመገንዘብ በቀሪ ቀናት አዲሱን ባርኮድ የተካተተበት ደረሰኝ ማሳተም የሚጠበቅባቸው መሆኑ ተገለፀ ።
ጥር 21 / 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ
በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ዑመር አብዳላ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት ” አሁን ላይ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ማንዋል ደረሰኝ ከየካቲት 02 / 2017 ዓ.ም ጀምሮ ጥቅም ላይ ስለማይውል ግብር ከፋዩ ይህን ተገንዝቦ ከወዲሁ አሳውቆ ወደ አዲሱ ደረሰኝ ህትመት እንዲገባ በርካታ የግንዛቤና የቅስቀሳ ስራዎች መሠራታቸውና አሁንም እንዳይዘናጉ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል ።
በቅርንጫፉ 1021 ደረሰኝ ተጠቃሚ ግብር ከፋዮች መኖራቸውን የገለፁት ሀላፊው 379 ግብር ከፋዮች አሳውቀው በብርሀን ሰላም ማተሚያ ድርጅት የህትመት ፈቃድ የወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል ።
ቀሪዎች 642 ግብር ከፋዮች አሁንም ሳይዘናጉና ላላስፈላጊ እንግልት ሳይዳረጉ ከወዲሁ አሳውቀው ደረሰኝ ህትመት እንዲያካሂዱ አሳስበዋል ።
ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ከደረሰኝ ህትመት ጋር ተያይዞ እስካሁን የሰራቸው ስራዎች በተመለከተ ሀላፊው እንደገለፁት በአካል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠቱና ለግንዛቤ የተዘጋጁ ብሮሸሮች፣ በራሪ ወረቀት በመስጠት ፣በቴሌ አጭር መልዕክት በመላክ ፣ በቅርንጫፉ ማህበራዊ የቴሌግራም ቻናል በመጠቀም ፣ በስልኮች በመደወል ጭምር እንዲያውቁ መደረጉን ተናግረዋል
ከገቢ አሰባሰብ አንፃር በበጀት አመቱ በስድስት ወራት 42.5 ቢሊየን ብር ለመሠብሰብ ታቀዶ፣ 39.02 ቢሊየን ብር የተሰበሰበ ሲሆን የዕቅዱን 92 ፐርሰንት ማሳካት መቻሉን ጠቁመዋል።
ለገቢ አሰባሰቡ ውጤታማነት የቢሮው አመራሮች ድጋፍና ክትትል ወሳኝ መሆኑን የገለፁት አቶ ዑመር ይህም ድጋፍ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል
በቀጣይም በበጀት አመቱ ቀሪ ወራት የበጀት ዐመቱን 75.2 ቢሊየን ብር ለማሳካትና ውጤታማ የገቢ አሰባሰብን ለማሳለጥ ቢሮው ያወረደውን የተከለሰ የ6ወራት ዕቅድ መነሻ በማድረግ ከማኔጅመንቱ ጋር በመወያየትና ከራስ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ወደ ተግባር መግባታቸውን ሀላፊው ገልፀዋል
በመሆኑም ደረሰኝ የማሳተም የህግ ግዴታ ያለባቸው የደረጃ ሀ እና ለ እንዲሁም በፈቃደኝነት ደረሰኝ የሚጠቀሙ የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች ጊዜው ሳይጠናቀቅ ወደሚከፍሉበት ቅርንጫፍ ፅ/ቤት በመምጣትና በማስፈቀድ ከብርሃና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ደረሰኙን ማሳተም የሚችሉ መሆኑ ተገልጿል ።
ይህ ሳይሆን ሲቀር ከየካቲት 2 ቀን 2017 ዓም ጀምሮ ነባሩን ደረሰኝ መጠቀም በህግ ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑም ተጠቁሟል ።
ግብርከፋዮች አሁንም ጊዜ አለን በሚል መዘናጋት ደረሰኝ ሳያሳትሙ ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት እንዳይዳረጉ ከወዲሁ በቀራቸው ቀናት አሳውቀው ደረሰኝ እንዲያሳትሙ ሀላፊው መልዕክታቸውን አስተላልፈውል ።