ነሐሴ 21 / 2017 ዓ / ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ባካሄደው የመኪና ላይ ኦፕሬሽን ያለደረሰኝ ግብይት ፈጽመው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 4 ተሸከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉ ተገልጿል።
በቢሮው በተካሄደ የመኪና ላይ ኦፕሬሽን በክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ስሙ ጀሞ አካባቢ ያለደረሰኝ ግብይት የተፈጸመ ሲሚንቶ ጭነው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 2 ሲኖትራክ፣ 1 ተሳቢ እና 1 ዳንጎቴ ተሸከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ፡፡
በቢሮው እንደተገለፀው በኦፕሬሽኑ ያለ ደረሰኝ ግብይት የተፈጸመበት 400 ኩንታል የሲሚንቶ ምርት የጫነ አንድ ተሳቢ ፣ 200 ኩንታል የጫኑ 2 ሲኖ ትራክ እና 350 ኩንታል ሲምንቶ የጫነ አንድ ዳንጎቴ መኪና በአጠቃላይ 950 ኩንታል ሲሚንቶ ተይዘው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል ፡፡
አያይዘውም 2 ሲኖትራክ ከተያዙ በኋላ ደረሰኝ በመቁረጣቸው በአዋጁ መሰረት አስተዳደራዊ እርምጃ የተወሰደ መሆኑንና 350 ኩንታል የጫነው ተሽከርካሪ በፓሊስ ቁጥጥር ስር እንዲሆን መደረጉን ጠቅሰዋል ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ወደከተማዋ የሚገቡ፣ከከተማዋ የሚወጡ እንዲሁም በከተማዋ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች፣ሚኒባሶችና ትናንሽ ሽፍን መኪኖች ልዩ ልዩ ምርቶችን ይዘው ሲንቀሳቀሱ በዕለቱ የተቆረጠ ደረሰኝ መያዝ እንዳለባቸው ማሳወቁ ይታወቃል።