ከአዲስ አበባ የሚወጡ እና የሚገቡ እንዲሁም በከተማዋ ወደተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ለጫኑት ዕቃ ህጋዊ ደረሰኝ እንዲቆርጡ የሚካሄድ ቁጥጥር ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለፀ።

ነሀሴ 25/ 2017 ዓ.ም : አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ወደ ከተማዋ የሚገቡና የሚወጡ እንዲሁም በከተማዋ ከቦታ ወደ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ለጫኑት ጭነት ህጋዊ ደረሰኝ ስለመያዛቸው ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

የቁጥጥሩን ስራ ሲያስተባብሩ የነበሩት በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የታክስ መረጃና የሽያጭ መመዝገቢያ አስተዳደር የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አለማየሁ አበራ የቁጥጥሩ ዋና ዓላማ ማንኛውም የተሽከርካሪ ባለቤትና አሽከርካሪ እንዲሁም ነጋዴ በተሽከርካሪዎች ላይ ጭኖ ለሚያጓጉዘው ዕቃ ህጋዊ የሆነ ዕለታዊ ደረሰኝ መያዝ እንደሚገባው ማስገንዘብ ነው ብለዋል ።

በዛሬው ዕለት የአራዳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከአራዳ ክፍለ ከተማ ፓሊስ ጋር በመቀናጀት በካቴድራል ፒያሳ ፣ በሀብተጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ ፣ በበኒን መስጂድ ፣ በጣሊያን ሰፈር ፣ በአራት መንታ ፣ በጎጃም በረንዳ እንዲሁም በኤሊያና ሞል አካባቢ የመኪና ላይ ጭነት ቁጥጥር አድርጓል ።

በዕለቱም የተለያዩ ዕቃዎችን ጭነው ሲንቀሳቀሱ በነበሩ 25 ተሽከርካሪዎች ላይ የተጫኑ ዕቃዎች ህጋዊ ደረሰኝ ያላቸው መሆኑን ፍተሻ የተደረገ ሲሆን 3 ያለደረሰኝ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ ህጋዊ ደረሰኝ ቆርጠው እንዲመጡ መደረጉ ተመላክቷል ።

ስለሆነም የተሽከርካሪ ባለቤትና አሽከርካሪ እንዲሁም ነጋዴ በተሽከርካሪዎች ላይ ጭኖ ለሚያጓጉዘው ማንኛውም ጭነት የጭነቱ ዋጋ ህጋዊ ደረሰኝ ፣ የተቆረጠው ደሰረኝ ከባለንግድ ፍቃዱ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ፣ የመጋዘን ፍቃድ ፣ የንግድ ፍቃድ ከመጋዘን ፍቃድ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ፣ የማጓጓዣ ( ደሊቨሪ ) ደረሰኝ እንዲሁም የንግድ ፍቃዱ የክፍለሀገር ከሆነ እዚህ ለመሸጥ የንግድ ፍቃድ ያስጠቀሰ መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎች መያዝ እንደሚገባው ተጠቁሟል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *