ነሀሴ 25/ 2017 ዓ.ም : አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የኮልፌ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ባካሄደው የቁጥጥር ስራ ዕለታዊ ደረሰኝ ሳይዙ ጭነት በመጫን ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ከመውሰድ ባሻገር ለጫኑት ዕቃ ደረሰኝ ማስቆረጡ ነው አሳውቋል።
የቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ የህግ ተገዢነት ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ብሩክታይት ባህሩ እንደገለፁልን ወደ ከተማዋ የሚገቡና የሚወጡ እንዲሁም በከተማዋ ከቦታ ወደ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ለጫኑት ጭነት ህጋዊ ደረሰኝ ስለመያዛቸው ቁጥጥር እየተደረገ ነው ።
እንደ ምክትል ስራ አስኪያጇ የቁጥጥሩ ዋና ዓላማ ማንኛውም የተሽከርካሪ ባለቤትና አሽከርካሪ እንዲሁም ነጋዴ በተሽከርካሪዎች ላይ ጭኖ ለሚያጓጉዘው ዕቃ ህጋዊ የሆነ ዕለታዊ ደረሰኝ መያዝ እንደሚገባው ማስገንዘብ ነው ብለዋል ።
በዛሬው ዕለት በክፍለ ከተማው በተለያዩ አካባቢዎች ከፓሊስ ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ዕቃዎችን ጭነው ሲንቀሳቀሱ በነበሩ 19 ተሽከርካሪዎች ላይ የተጫኑ ዕቃዎች ቁጥጥር የተደረገ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 5 ያለደረሰኝ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ ህጋዊ ደረሰኝ ቆርጠው እንዲመጡ መደረጉ ተመላክቷል ።
ስለሆነም የተሽከርካሪ ባለቤትና አሽከርካሪ እንዲሁም ነጋዴ በተሽከርካሪዎች ላይ ጭኖ ለሚያጓጉዘው ማንኛውም ጭነት የጭነቱ ዋጋ ህጋዊ ደረሰኝ ፣ የተቆረጠው ደሰረኝ ከባለንግድ ፍቃዱ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ፣ የመጋዘን ፍቃድ ፣ የንግድ ፍቃድ ከመጋዘን ፍቃድ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ፣ የማጓጓዣ ( ደሊቨሪ ) ደረሰኝ እንዲሁም የንግድ ፍቃዱ የክፍለሀገር ከሆነ እዚህ ለመሸጥ የንግድ ፍቃድ ያስጠቀሰ መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎች መያዝ እንደሚገባው ተጠቁሟል ።