ቢሮው አመራሮችና ሰራተኞች በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ተሳትፎና በአመራሮቿ ቁርጠኛነት አቋም የታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ እንዳስደሰታቸው ገለፁ፡፡

መስከረም 5/ 2015 ዓ. ም : አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በዛሬው ዕለት ” የህዳሴ ግድባችን የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት ነው ” በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ውይይት አካሄዷል ።

በውይይት መድረኩ የታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የኢትዮጵያን ከፍታ ከማሳየቱ ባሻገር የብሔራዊ መግባባት እና አንድነትን የሚያሳይ መሆኑ ተገልፆል፡፡

የውይይቱን መድረክ የከፈቱት በቢሮው የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዳነ ሱሌ ዓላማው በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት የተሰራና የተጠናቀቀ በመሆኑ ሁሉም ማህበረሰብ የደስታው ተካፋይ መሆን ስለሚገባ ነው ብለዋል ።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ሀገራዊ መነቃቃትን የፈጠረ ፣ የይቻላል መንፈስን እንድንላበስ ያስቻለ ፣ ሀገራዊ መግባባትን ያጎለበተ ፣ ለቀጣይ ልማቶቻችን ማስቀጠያ እና ሀገራዊ ግንባታን በማሳደግ መስራት የሚያስችል አቅም እንዳለ ለሀገራት ማሳያ የሆነ መሆኑን አቶ አዳነ ገልፀዋል ።

በቀጣይ በታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የተፈጠረውን መነሳሳት በመጠቀም እንደሀገር ብሎም እንደከተማ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በጋራና በአንድነት ወደ ውጤት መቀየር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል ።

በውይይቱ መድረኩ የተሳተፉ አመራሮችና ሰራተኞች የ14 ዓመታት የፅናት አርማ የሆነው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ መላው ኢትዮጲያዊ ያለ ልዩነት ሊደሰት ይገባል ብለዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ የህዝቦች የአንድነት፣ የኅብረት መሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው ያሉም ሲሆን ከህዳሴ ግዱ ተምረን በቀጣይ እንደሀገርና ከተማ የተያዙ ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ በአንድነት መቆም ይገባልም ብዋል፡፡

ብዙ ውጣ ውረዶች ያለፈው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በላቀ ድምቀት ለምረቃ በመብቃቱም ከጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ለፕሮጀክቱ ስኬት የተገቡ አመራሮችና መላው የኢትዮጲያ ህዝብ እንኳን ደስ አለን፣ አላችሁ! ሲሉም ደስታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *