መስከረም 9 ቀን 2017ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፣ገቢዎች ቢሮ
በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ለቅርንጫፍ ፅ/ቤት የበጀትና ዕቅድ ክትትልና ድጋፍ የስራ ሂደቶችና ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቷል፡፡
የስልጠና መድረኩን የከፈቱት የቢሮው ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ በየደረጃው ያለው የእቅድ ክፍል ጥራት ያለው፣ ፈጣንና በአግባቡ የተደራጀና የተተነተነ መረጃ ለውሳኔ በማቅረብ የተቋሙ ዕቅድ እንዲሳካ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
ከትክክለኛና ጥራት ካለው መረጃ ውጪ የሚወሰን ማንኛውም ውሳኔ ለስህተት የሚዳርግ ነው ያሉት ኃላፊ በዚህ ረገድ የዕቅድ ባለሙያዎች የተቋሙ የጀርባ አጥንት በመሆን ስራዎቻቸውን በአግባቡ መፈፀም እንደሚጠበቅባቸውም አሳሰበዋል፡፡
በተለይም በቅርንጫፍ ደረጃ የሚገኙ ባለሙያዎች ለአመራሮቻቸው የተደራጀና የተተነተነ መረጃ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው በማንሳት የሚቀርቡ መረጃዎች ተከታታይነትና ወጥነት ያላቸው ሊሆኑ ይገባልም ብለዋል፡፡
የገቢ ተቋምን ትክክለኛ ባልሆነ፣ ጥራት በጎደለውና ቁንፁል በሆነ መረጃ መምራት እንደማቻል በመግለፅም ባለሙያዎች ለቅርንጫፍ ፅ/ቤት አመራሮች ጥልቀት ያለውና በአግባቡ የተደራጀና የተተነተነ መረጃ የማቅረብ ሚናቸውን በተገቢው ደረጃ ሊወጡ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ለዚህ በማዕከል ያለው የበጀትና ዕቅድ ዳይሬክቶሬት የቅርንጫፍ ባለሙያዎችን አቅም ቀጣይነት ባለው ደረጃ በመገንባት የክህሎት ክፍተቶችን ለመሙላት አቅዶ መስራት ይጠበቅበታል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በዕለቱ ከቅርንጫፍ ፅ/ቤት ለተውጣጡ ከ70 በላይ ለሚሆኑ የስራ ሂደቶችና ባለሙያዎች በኢቲ-ታክስ እና በዳታቤዝ አጠቃቀም እንዲሁም በዕቅድ አስተቃቀድና ሪፖርት አዘገጃጀት ላይ ሰልጠና ተሰጥቷል፡፡