ቢሮው በጥር ወር 10 ነጥብ 79 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 12 ነጥብ 73 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 118 በመቶ ማሳካቱ ተገለፀ፡፡
የካቲት 6 ቀን 2017ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፣ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በበጀት ዓመቱ ጥር ወር 10 ነጥብ 79 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 12 ነጥብ 73 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 118 በመቶ ማሳካቱ ተገለፀ፡፡
ይህ የተገለፀው የቢሮው የዕቅድና ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት የጀነራል ካውንስል አባላት በተገኙበት የበጀት ዓመቱን የሰባት ወራት የገቢ ዕቅድ አፈፃፀምን በማቅረብ ውይይት በተካሄደበት መድረክ ነው፡፡
በመድረኩ የቢሮው ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ የተቋሙ የገቢ የዕቅድ አፈፃፀም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለና ዕድገት እያሳየ መጥቷ ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያም በገቢዎች ቢሮ በበጀት ዓመቱ 7 ወራት 103 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 98ነጥብ 81 በመሰብሰብ የዕቅዱን 95.37 በመቶ ለማሳካት መቻሉን ተጠቁሟል፡፡
የዕቅድ አፈፃፀሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር የ43.41 በመቶ ወይም የ29.91 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩልም በበጀት ዓመቱ ከሀምሌ አስከ ጥቅምት ወራት ያልተሰበሰበ በድምሩ 11 ነጥብ 29 ቢሊዮን ብርን በህዳር፣ታህሳስ እና ጥር ወራት በተከናወኑ ተግባራት 6 ነጥብ 49 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መቻሉን ቀሪ ውዝፍ ዕዳ ወደ 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለማውረድ ተችሏልም ብለዋል፡፡
በሰባት ወራት ሊሰበሰቡ የሚችሉ ገቢዎችን አሟጦ ማሰባሰብ ቢቻል ኖሮ ዕቅዱን ከዚህም በላይ ማሳካት ይቻል ነበር ያሉት ኃላፊ ለዚህ ውጤት በተወሰኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ያጋጠሙ የአመራር ትኩረት ማነስ ፣ የቅንጅታዊ አሰራር ክፍተት ፣ እንደቢሮ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት አለመፈፀም እነደ ምክንያት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
በመጨረሻ የአመራር ብቃትና ክህሎትን በማሳደግ እንደቢሮ በሁሉም የሚወርዱ አሰራሮችን በወጥነት በመተግበር ከተማዋ የምታመነጨውን ኢኮኖሚ አሟጦ በመሰብሰብ ቢሮው የተጣለበትን ኋላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ ሁሉም አመራርና ፈፃሚ ትኩረት ሰጥቶ መሰርታ እንደሚገባው አስገንዝበዋል ።
በመድረኩ የዕቅድ አፈፃፀሙ ሪፖርት በቢሮው የዕቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ግርማ የቀረበ ሲሆን ከመድረኩ ለተነሱ ጥያቄዎችና ፣ አስተያየቶች እና ምላሽ ለሚሹ ጉዳዬች በቢሮው ሃላፊና በሚመለከታቸው የዘርፍ ሃላፊዎች እንዲሁም ዳይሬክቶሬቶች ምላሽ ተሰጥቷል ።