ቢሮው ለከተማዋ ልማት የሚውል ገቢን በፍትሃዊነት ለመሰብሰብና ከግብር ከፋዩ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ከታማኝ ግብር ከፋዮች ጋር በቅንጅት የሚሰራ መሆኑ ተገለፀ፡፡

ታህሳስ 7 ቀን 2018ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፣ ገቢዎች ቢሮ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በዛሬው ዕለት ከ2017 የግብር ዘመን የፕላቲኒየምና የወርቅ ደረጃ ተሸላሚ ታማኝ ግብር ከፋዮች ጋር በተቋሙ እየተከናወኑ በሚገኙ የሪፎርም ተግባራት ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩ በቢሮው ፍትሀዊ የገቢ አሰባሰብ ስርአትን ለማስፈንና ብልሹ አሰራርን ስርአት ለማስያዝ እየተከናወኑ የሚገኙ የሪፎርም ተግባራት እና የተገኙ ውጤቶች፣ አሁንም የሚስተዋሉ የአፈፃፀም ክፍተቶችና ክፍቶቹን ለማረም በአደረጃጀት፣ በአሰራር፣ በቴክኖሎጂ ልማትና በሰው ኃይል ግንባታ ረገድ በተወሰዱ እርምጃዎች ዙሪያ ገለፃ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የመድረክ ተሳታፊዎችም ቢሮው ከግብር ከፋዮች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት መድረኩን ማመቻቸቱ የሚያስመሰግነው ተግባር ነው ካሉ በኃላ በቴክኖሎጂ ልማት፣ በአሰራር፣ በህግ ማስከበር እየተከናወኑ በሚገኙ ተግባራት የተሻሉ ለውጦች መመልከት ጀምረናል ብለዋል፡፡

ይሁንና ከፌዴራል ጉሙሩክ ኮምሽን አሰራር፣ ከገበያ ዋጋ ጥናት፣ ከደረሰኝ አጠቃቀም፣ ከቫት ማሳወቂያ መስተንግዶ ፕሮግራም፣ ከባለሙያዎች ስነ ምግባር፣ ከታክስ ህጎች ግንዛቤ ፈጠራ አኳያ ክፍተቶች መኖራቸውም አንስተዋል፡፡

በታማኝ ግብር ከፋዮች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን የከተማዋን ልማት ቀጣይነት ለማረጋገጥና ተወዳዳሪነቷን ለማጎልበት ገቢን የመሰብሰብ አቅምን ማጎልበት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የከተማዋ ገቢ ከለውጡ ወዲህ በየዓመቱ ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ ቢሆንም የከተማዋ ኢኮኖሚ ሊያመነጭ ከሚችለው ገቢ አኳያ ግን አሁንም ብዙ መስራት ይገባልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የከተማዋ ብቸኛ የገቢ መሰረት ከግብር ከፋዮች የሚሰበሰብ ግብር ነው ያሉት አቶ አብዱልቃድር ቢሮው ተልዕኮውን በአግባቡ ለመወጣት የተለያዩ አሰራሮች በመፈተሽ ለማስተካከል፣ አዳዲስ አደረጃጀቶችን በጥናት በመለየት ለመፍጠር እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን ለማልማት የተደረጉ ጥረቶች አበረታች ውጤት የታዩባቸው መሆናቸውም ገልፀዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩም የሚሰበስበው ገቢ በአግባቡና በቁጠባ ከመጠቀም አኳያም የገቢውን 72 በመቶ ለካፒታል ፕሮጀክቶች፣ ለማህበራዊ ልማት፣ ለድህነት ቅነሳ ስትራቴጂዎች ማስፈፀሚያና ለሰው ተኮር የልማት ስራዎች እያዋለ ይገኛልም ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም አስተዳደሩ ስማርት ሲቲ ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ መሆኑን በመግለፅ በገቢዎች ቢሮ በቅንጅት ለምተው ወደ ተግባር የተሸጋገሩ ቴክኖሎጂዎች የዚህ ጥረት አካል ናቸው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ በበኩላቸው ቢሮው በግብር ከፋዮች ከመልካም አስተዳደርና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች ለመቅረፍ ከግብር ከፋዮች ጋር በጋራ በመተጋገዝ መንፈስ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ቢሮው ወደ ተግባር ያሸጋገረው የገበያ ዋጋ ጥናት ተጠቃሚ የሚያደርገው በዋናነት ህጋዊ ነጋዴንና ግብር ከፋዩን ነው ያሉት ኃላፊው ይሁንና በአፈፃፀም ረገድ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

በከተማዋ ከደረሰኝ ግብይት ጋር በተያያዘ ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉ ከታማኝ ግብር ከፋዮች የተነሳው ሃሳብ ትክክል እንደሆነ በመግለፅም ቢሮው ችግሩን በመረዳት ለመቅረፍ የቁጥጥር ስራዎች በበር ለበር፣ በመጋዘንና በተሸከርካሪዎች ላይ በቴክኖሎጂ ተደግፈው እንዲተገበሩ አድርጓል ብለዋል፡፡

ቢሮው በከተማዋ ፍትሃዊ የግብር አሰባሰብ ስርዓት ለማስፈን፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል እንዲሁም የታክስ መሰረትን ለማስፋት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል፡፡

ከባለሙያዎች ስነ ምግባር ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮች ለመቅረፍ ጠንካራ የተጠያቂነት ስርዓት በመዘርጋት ወደ ተግባር አሸጋግሯል ያሉት አቶ ቢኒያም በቀጣይም ከግብር ከፋዮች ጋር በጋራ በቅንጅት በመስራት ችግሩን በተሟላ ደረጃ ለመቅረፍ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ቢሮው በ2017 የግብር ዘመን የታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና ፕሮግራም ላይ በከተማዋ ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ለታማኝ ግብር ከፋዮች በተገባ ቃል መሰረት በከተማ አስተዳደሩ ስር በሚገኙ ተቋማት ለታማኝ ግብር ከፋዮች የአገልግሎት ቅድሚያ መጠቀሚያ VIP ካርድ ተበርክቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *