በመዲናዋ በተሽከርካሪ ጎማዎች ንግድ በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ በተካሄደ የታክስ ኦፕሬሽን በ11 የንግድ ድርጅት ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ የተገኙ 15 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡

ታህሳስ 11 ቀን 2018ዓ.ም ፣ አዲስ አበባ፣ ገቢዎች ቢሮ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች የተሸከርካሪ ጎማ በሚሸጡ የንግድ ድርጅቶች ላይ ባካሄደው የኦፕሬሽን ተግባር ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ የተገኙ 15 ግለሰቦችን በህግ ቁጥጥር ስር ማዋሉን አሳውቋል፡፡

በዛሬው ዕለት ቢሮው ያካሄደው ድንገተኛ የኦፕሬሽን ተግባር ለረጅም ቀናት በተካሄደ ጥናት ላይ የተመሰረተ ሲሆን በቁጥጥር ስር የዋሉት 15 ከፍተኛ እና መካከለኛ የመኪና ጎማ የሚሸጡ ነጋዴዎች ናቸው፡፡

ግለሰቦቹ የመንግስትን ግብር ለመሰወር ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ ተገኝተው በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸውን የገለፀው ቢሮው የኦፕሬሽን ተግባሩ መርካቶን ጨምሮ በተመረጡ 12 የከተማዋ የጎማ መሸጫ ቦታዎች ላይ ማከናወኑን ተገልፆል፡፡

ቢሮው የኦፕሬሽን ተግባሩን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ያካሄደ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ግለሰቦቹ በአሁኑ ወቅት የመንግሰትን ጥቅም ለማሳጣት ከግብር ህግ ጋር በተፃረረ መልኩ ያለደረሰኝ ሽያጭ በመፈፀም በተፈፀመ ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፖሊስ ተይዞ ለፍርድ የሚቀርቡ ይሆናል ብሏል፡፡

ቢሮው የኦፕሬሽን ተግባሩ በቀጣይ ቀናት በሌሎችም ዘርፎች አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያሳወቀ ሲሆን የንግዱ ማህበረሰብ ግብይቶችን በደረሰኝ ብቻ እንዲፈፅም ህብረተሰቡም በ7075 ነፃ የስልክ መስመር በመጠቀም መሰል ወንጀሎችን እንዲያጋልጥ ተጠይቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በታክስ አስተዳደር አዋጅ 983/2008ዓ.ምመሰረት በከተማችን የሚፈፀሙ ህገ-ወጥ ግብይቶችን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *