መጋቢት 04 / 2018 ዓ / ም የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2018 በጀት ዓመት በውስጥ ባለሙያዎች አቅምና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በርካታ ቴክኖሎጂዎችን በማልማትና ወደ ተግባር በማሸጋገር የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን የሚያስችሉ ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱ ይታወቃል ፡፡
በዚህ መነሻነትም ቢሮው በዛሬው ዕለት ከፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር እና ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት (GIZ) ጋር በቴክኖሎጂ ልማትና በአቅም ግንባታ ዘርፎች በጋራ ለመስራት የሚያስችል ውይይት አካሂዷል።
በቢሮው የሞደርናይዜሽን ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ አብዱራህማ እንደገለጹት የፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር ከGIZ ጋር በመተባበር በፕሮጀክት ደረጃ ቢሮውን በቴክኖሎጂ ልማት ለመደገፍ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በውይይቱ ቢሮው በአደረጃጀት፣ በቴክኖሎጂ ልማት እየተካሄዱ በሚገኙ በሪፎርም ተግባራት የተገኙ ውጤቶች፣ በአፈፃፀም የሚስተዋሉ ክፍተቶችና ክፍተቶቹን ለመቅረፍ እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሄ እርምጃዎች ላይ ማብራሪያ መሰጠቱን አክለው ገልፀዋል፡፡
አክለውም በቢሮው የሚሰጡ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ በማስቻል ውጤታማ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትና በቀጣይ በቢሮው ለማልማት የታቀዱ ቴክኖሎጂዎች ላይ ውይይት መካሄዱ አመላክተዋል፡፡
በቀጣይም ከጂአይዜድ እና ከፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት በመስራት እና በፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር የለሙ እና ወደ ተግባር የተሸጋገሩ ቴክኖሎጂዎችን ከከተማው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ለመተግበር የሚሰራ ይሆናል ብለዋል፡፡
በፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ስርዓት ማጣጣምና የክልልና የከተማ አስተዳደር ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሐኑ አበበ በበኩላቸው፣ የውይይቱ ዋና ዓላማ የገቢ ተቋማትን አቅም ለመገንባት ከተመረጡ ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አንዱ በመሆኑ ከGIZ የሚሰጠውን ድጋፍ ለመወያየት መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም በቢሮው ያሉ ጥንካሬዎችና ክፍተቶች መቅረባቸውን ጠቅሰው፣ በኦዲት ስራዎች፣ በመረጃ ትስስር፣ በስጋትን መሰረት የሚካሄዱ የኦዲት ስራዎች እና በአጠቃላይ የታክስ አስተዳደር ማዘመን ስራዎች ከከተማው ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዴት ሊጣጣሙ እንደሚገባ መወያየታቸውን ገልጸዋል።
በGIZ የታክስ አድሚንስትሬሽን ሪፎርም አማካሪ አቶ ማርከስ ፓፍዛን እና የፕራይቬት ሴክተር አማካሪ ወይዘሮ እመቤት ተስፋዬ በበኩላቸው፣ ቢሮው በተለይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አንጻር ጥሩ ስራዎች መሰራታቸውን ከቀረበላቸው ሰነድ እና በቦታ በማየት መረዳታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም ከፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ልማት፣ በአቅም ግንባታ ስራዎች እና በሌሎች የሪፎርም ዘርፎች በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ቢሮው በቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት ( GIZ) ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችል ውይይት አካሄደ፡፡
