በትምህርት ቤቶች የታክስ ክበባትን በማጠናከር ግብሩን በታማኝነትና በፍቃደኛነት ለመክፈል ዝግጁ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ መሆኑ ቢሮው ገለፀ ።
መጋቢት 10 /2017 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፣ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና ከፋና ብሮድካቲንጋ ጋር በነበረው ቆይታ ሌብነትን በመጠየፍ ግብርን በፍቃደኛነት የሚከፍል ትውልድ የማፍራት ስራ ከትምህርት ቤቶች ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑ ተገልጿል ።
የቢሮው የህግ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ሚኪያስ ሙሉጌታ በዛሬው ዕለት ከሚዲያዎቹ ጋር በነበራቸው ቆይታ የአንድ አገር የታክስ ስርዓት የህዝብና የመንግስት ግንኙነት ከሚገለፅባቸው አበይት መንገዶች መካከል አንዱ መሆኑን ገልፀው ይህንንም የበለጠ ለማጎልበት በከተማዋ ከሚገኙ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር የታክስ ክበባትን በማቋቋም በነገ አገር ተረካቢ ዜጎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እየተሰራ ነው ብለዋል ።
ቢሮው በትምህርት ቤቶች በታክስ ክበባት አማካይነት ግብር ለአንድ አገር ያለውን ጠቀሜታ የተገነዘበና ፍቃደኛ የሆነ ግብር ከፋይ ህብረተሰብን ለመፍጠር ብዙ ስራዎች እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
አክለውም ግብርን በፈቃደናነትና በታማኝነት የመክፈል አሰባሰብና ባህል በማዳበር ሌብነትን የሚጸየፍ ትውልድ መፍጠር የሚቻለው ተማሪዎች ከህጻንነት ጀምሮ ስለ ግብር ጠቀሜታ እንዲረዱና ግንዛቤ እንዲጨብጡ በማድረግና አዲሱን ትውልድ ስለ ግብር በጎ አመለካከት እንዲኖረው ማድረግ ሲቻል እንደሆነ አስገንዝበዋል ።
በትምህርት ቤቶች የታክስ ክበባትን ለማጠናከር የሚነበቡ ሞጁሎች ፣ በራሪ ወረቀቶች እነዲሁም ለክበቡ አባላት ስልጠና ከመስጠት ባሻገር በትምህርት ቤቶች መካከል ውድድሮችን በማድረግ ተደራሽነቱን የማስፋት ስራዎች እየተሰራ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በትምህርት ስርዓት ውስጥ እራሱን ችሎ እንዲሰጥ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ስራዎች እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል ።
በቀጣይ በትምህርት ቤቶች የተጀመሩ የታክስ ክበባትን የበለጠ በማጠናከር የተማሪዎች ግንዛቤን ከመሠረቱ በማነፅ የግብር ጉዳይ ላይ ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር የሚያስችሉ ስራዎችን አጠናክረን እንሰራለን ሲሉ ሃላፊው ተናግረዋል ።