<<የልኳንዳ ቤት አስተናጋጁን ደረሰኝ አልቆረጥክም>> በሚል አስፈራርተው የ15 ሺህ ብር ጉቦ ለመቀበል ከተደራደሩ 3 የቁጥጥር ባለሙያዎች አንዱ እጅ ከፍንጅ ሲያዝ 2ቱ ሮጠው በማምለጣቸው በፖሊስ ክትትል እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ።
ሚያዚያ 24 ቀን 2017ዓ.ም ፣ አዲስ አበባ፣ ገቢዎች ቢሮ
የኮልፌ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የቁጥጥር ባለሙያዎች የሆኑ አቶ መስፍን አወቀ፣ አቶ ዘርሁን ዘርዓ እና አቶ ገለቱ አወቀ የተባሉ 3 ተጠርጣሪዎች ሚያዚያ 18 ቀን 2017ዓ.ም በተለምዶ ዓለም ባንክ እየተባለ በሚጠራ አካባቢ ከሚገኝ ስጋ ቤት የ15 ሺህ ብር ጉቦ ለመቀበል በመደራደር ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ ገንዘቡን ከተቀመጠበት ሱቅ ሲቀበል በቁጥጥር ስር ሊውል መቻሉ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ አሳውቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በክፍለ ከተማው ወረዳ 4 የደረሰኝ ቁጥጥር እንዲያደርጉ የተመደቡ ይሁን እንጂ በመንግስት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ጉቦ ለመቀበል አስፈራርተው በመደራደር ከመካከላቸው አንዱ ገንዘቡን ሲቀበል ነው እጅ ከፍንጅ ሊያዝ የቻለው፡፡
እንደ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ መረጃ ተጠርጣሪዎቹ ዓለም ባንክ አካባቢ ‹‹ዐሼ ስጋ ቤት›› ከሚባል ምግብ ቤት በመግባት አስተናጋጁ ምግብ በፌስታል ይዞ ሲወጣ ደረሰኝ አልቆረጥክም በሚል በማስፈራራት የጠየቁትን ገንዘብ ካልተሰጣቸው ምግብ ቤቱ እንደሚታሸግና የ100 ሺህ ብር ቅጣት እንደሚቀጣ በማስፈራራት 15 ሺህ ብር ተደራድረው ገንዘቡን በአካባቢው ከሚገኝ ሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ እንዲያስቀምጥ ትዕዛዝ መስጠታቸው ተገልፆል፡፡
በኃላም አስተናጋጁ ማስፈራሪያው በፈጠረበት ስጋት በመደናገጥ የተጠየቀውን 15 ሺህ ብር ጉቦ በተባለው ሱቅ ያስቀመጠ ሲሆን ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አቶ ዘርሁን ዘርዓ የተባለው ግለሰብ ገንዘቡን ከሱቁ ተቀብሎ ሲቆጥር እጅ ከፍንጅ መያዙን ተገልፃል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ አስተናጋጁን በማዋከብ ሲያስፈራሩ በነበረበት ወቅት ምግብ በመመገብ ላይ የነበሩ ሲቪል የፖሊስ አባላት ጉዳዮን እስከመጨረሻ በመከታተል ከተጠርጣሪዎች መካከል አንዱ ከነገንዘቡ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውና 2ቱ በወቅቱ በመሮጥ ማምለጣቸው የደረሰን መረጃ ይጠቁማል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ፖሊስ ከ3ቱ ተጠርጣዎች አንዱን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራውን የቀጠለ 2ቱ ተባባሪዎቹን ለመያዝ ክትትሉን መቀጠሉ ታውቋል።