ቢሮው ከ149 ሚሊዮን ብር በላይ የታክስ ዕዳቸውን ያልከፈሉ 8 ተጨማሪ ግብር ከፋዮች ከሀገር እንዳይወጡ የእግድ ትዕዛዝ መተላለፉ ገለፀ፡፡
ከዚህ ቀደም ከታገዱ 62 ግብር ከፋዮች 3ቱ ግብራቸውን በመክፈላቸው የጉዞ እግዱ እንዲነሳ መደረጉም ተጠቁሟል።
መጋቢት 10 / 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ለከተማዋ ልማት ሊውል የሚገባውን 149 ሚሊዮን 939 ሺህ 566 ብር የግብር ዕዳ ያለባቸው 8 ግብር ከፋዮች በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀፅ 44 ንዑስ አንቀፅ ከ1-3 በተሰጠው ስልጣን መሰረት ከሀገር እንዳይወጡ ለፌዴራል የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዝርዝራቸውን ማስተላለፉን አሳውቋል፡፡
በየካቲት ወር መጨረሻ ከ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የግብር ዕዳ ያለባቸው 62 ግብር ከፋዮች ከሀገር እንዳይወጡ የእግድ ትህዛዝ ማስተላለፉ ቢሮው በማስታወስ ከእነዚህ ውስጥ 3ቱ የግብር ግዴታቸውን ለመክፈል ተስማምተውና የጊዜ ስምምነት በመውሰድ ዕዳቸውን መክፈል በመጀመራቸው እግዱ እንዲነሳ ማድረጉም ገልፆል፡፡
ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል ለከተማዋ ሁለንተናዊ እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክትም ቢሮው ጥሪውን አስተላልፏል፡፡