በመርካቶ የገበያ ስፍራ በደረሰኝ ቁጥጥር ላይ የተጀመሩ ተግባራትን ለማጠናከር የሚረዳ ውይይት ተካሄደ
ሕዳር 04 / 2017 ዓ / ም የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ፣ በፌደራል ገቢዎች ሚንስቴር እና በፌደራል ጉምሩክ ኮሚሽን በደረሰኝ ቁጥጥር ላይ የተጀመሩ ተግባራት ለማጠናከር የሚረዳ የጋራ ውይይት ተካሄደ፡፡
በዛሬው ዕለት በተካሄደው በዚሁ ውይይት በከተማ አስተዳደሩና በፌደራል ተቋማቱ የተጀመሩ የደረሰኝ ቁጥጥር ተግባራት ውጤታማነት ለማጎልበት በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑ መግባባት ላይ ተደርሷል ።
ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ በገቢ ዘርፍ የሚስተዋሉ ያለ ደረሰኝ ግብይቶችን ለመቆጣጠር የፌዴራል ተቋማቱ በትብብርና በቅንጅት መስራታቸው ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተጠቁሟል።
በተለይ በመርካቶ አካባቢ በአስመጪዎች፣ በአከፋፋዮችና በቸርቻሪ ነጋዴዎች የሚካሄድ ያለደረሰኝ ሽያጭ ለማስተካከል ከፌደራል ገቢዎች ሚንስቴር፣ ከጉምሩክ ኮሚሽንና ከኦሮሚያ ክልል ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባም የጋራ መግባባት ተፈጥሯል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ በመሩት በዚሁ የውይይት መድረክ በፌዴራል ገቢዎች ሚንስቴር የታክስ ማጭበርበር ምርመራ ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ገዙ፣ ከፌደራል ጉምሩክ ኮሚሽን የኮንትሮባንድና የድንበር አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ተገኔ ደረሰ እና የኢንተሊጀንስ ዳይሬክተር አቶ ሰኚ አሰፋ ተሳትፈዋል ።
ውጤታማ የገቢ አሰባሰብ ለአዲስ አበባ ብልጽግና