በመዲናዋ የሚፈፀሙ ግብይቶች በህጉ መሠረት በደረሰኝ ብቻ በመፈፀም ህገወጥነትን መከላከል ይገባል :- አቶ ዣንጥራር አባይ

በመዲናዋ የሚፈፀሙ ግብይቶች በህጉ መሠረት በደረሰኝ ብቻ በመፈፀም ህገወጥነትን መከላከል ይገባል :- አቶ ዣንጥራር አባይ
ህዳር 10 / 2017 ዓ. ም : አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኑሮ ውድነትና ህገወጥነት የመከላከል ግብረኃይል በትላንቱ ዕለት በመዲናዋ በመርካቶ ከሚገኙ ነጋዴዎች ጋር በደረሰኝ ግብይትና በህገወጥ ንግድ እንቅስቃሴ ላይ ውይይት አካሂዷል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ፣ የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊና የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ አቶ ዣንጥራር አባይ በመዲናዋ የሚካሄዱ ግብይቶች በታክስ ህጉ መሰረት በደረሰኝ ላይ መመስረት አለባቸው ብለዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ መዲናዋ ለጀመረቻቸው ልማቶች ዋነኛ የጀርባ አጥንት መሆናቸውን የገለፁት ኃላፊው የከተማዋን ብልፅግና ለማስቀጠል ግብይቶችን በደረሰኝ ማካሄድ ይገባልም ብለዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ ግብይቱን በደረሰኝ በመፈፀም የከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ዘመናዊና ህጋዊ በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል ።
በከተመዋ የተጀመሩ የልማት ተግባራትና ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በታቀደው ደረጃ ሊጠናቀቁ የሚችሉት ከተማዋ ማመንጨት የምትችለውን ገቢ አሟጦ መሰብሰብ ሲቻል መሆኑን የገለፁት ም/ከንቲባውና የግብረኃይሉ ሰብሳቢ አቶ ዣንጥራር አባይ የደረሰኝ ግብይት ደግሞ ለገቢ አሰባሰቡ ቁልፍ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ስለሆነም የንግዱ ህብረተሰብ ከደረሰኝ ጋር በተያያዘ የተጀመረው ቁጥጥር ወደኃላ የማይመለስ መሆኑን በመገንዘብ ህግ አክብሮ ግብይቱን በደረሰኝ ብቻ ሊፈፅም እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ኋላፊ አቶ ቢንያም ምክሩ በበኩላቸው በመርካቶ ከደረሰኝ ግብይት ጋር በተያያዘ በአምራቾች ፣ በአስመጪዎች፣ በአከፋፋይና በቸርቻሪ ነጋዴዎች ቁጥጥሮች መጀመራቸው በመግለፅ እየተካሄደ ያለው ቁጥጥር ይበልጥ እየተጠናከረ የሚቀጥል መሆኑን አስረድተዋል።
ቢሮው ከአስመጪዎች፣ ከአከፋፋዮችና ከአምራቾች ጋር በተያያዘም የሚደረጉ ቁጥጥሮችን ለማጠናከር የሚያቀርቡትን የሂሳብ ሰነድ ፣ የፋብሪካ ዋጋ መረጃ ፣ የጉምሩክ መረጃና ከዋጋ በታች የሚቀርቡ ደረሰኞችን የማጣራት ስራዎች እያከናወነ ይገኛልም ብለዋል።
በዚህም ቢሮው ከእነዚህ አካላት በገቢ ጥናት ላይ በተመረኮዘ ዋጋ መነሻ ታክስ እንዲከፍሉና ደረሰኝ እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብለዋል ።
ቸርቻሪ ነጋዴዎችም ይህንን በጎ ተግባር ለማሰቀጠል ደረሰኝ ላይ የተመረኮዘ ግብይት በማካሄድና ደረሰኝ የማይሰጡትን አምራቾች ፣ አስመጪዎች እንዲሁም አከፋፋይ ነጋዴዎች ማጋለጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተሚ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው በከተማዋ የሚስተዋል ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመቅረፍ በሚደረግ ጥረት የንግድ ማህበረሰብ ሚናውን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
ውጤታማ ገቢ አሰባሰብ ! ለአዲስ አበባችን ብልፅግና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *