መዲናዋ ከደረሰኝ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለፀ ።
ሕዳር 10 / 2017 ዓ. ም : አዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ
በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ፣ በፌደራል ገቢዎች ሚንስቴርና በጉምሩክ ኮሚሽን በጋራ በተዘጋጀው መድረክ በደረሰኝ ግብይት ዙሪያ በመርካቶ ከሚገኙ አምራቾች፣ አስመጪዎች እና አከፋፋዮች ጋር ውይይት ተካሄዷል ።
የውይይት መድረኩ የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ፣ በጉምሩክ ኮሚሽን የሕግ ተገዢነት ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ባዘዘው ጫኔ እና በፌደራል ገቢዎች ሚንስቴር የሚንስትሩ አማካሪ አቶ ጌታቸው ደገፋ ናቸው።
አቶ ቢኒያም በከተማው የተጀመረው ልማት ቀጣይነት ሊኖረው የሚችለው ገቢን በብቃት መሰብሰብ ሲቻል መሆኑን ጠቅሰው ቢሮ ገቢን በብቃት እንዳይሰበሰቡ የሚያደርጉ ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች ለይቶ እየፈታ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት ከንግዱ ማሕበረሰብ የሚሰበስበው ገቢ መልሶ የንግዱ ማሕበረሰብ በሚጠቅሙ ልማቶች ላይ እያዋለ መሆኑን የተለያዩ አብነቶችን በመጥቀስ የገለጹት ኃላፊው ገቢን በብቃት እንዳይሰበሰቡ ከሚያደርጉ ውጫዊ ተግዳሮቾች መካከል ያለደረሰኝ የሚፈጸም ግብይት ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቢሮው ከደረሰኝ ግብይት ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ችግሮችና ምንጫቸውን በጥናት መለየቱን ጠቅሰው ችግሮቹን ለመቅረፍ ከገቢዎች ሚንስቴር፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከኦሮሚያ ክልልና ከሸገር ከተማ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመጨረሻም ታክስ ከፋዮ ሕብረተሰብ ያለደረሰኝ ግብይት ለመፈጸም የሚቀርባቸው ምክንያቶች ዋጋ የሌላቸው በመሆኑ ጊዜው ሳያባክን የሚያካሄዳቸው ግብይቶች በታክስ ህጉ መሰረት በደረሰኝ ላይ ብቻ መመስረት አለበት ብለዋል።
የፌደራል ጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ባዘዘው ጫኔ በበኩላቸው ሐገራችን በአፍሪካ ብዙ የሕዝብ አቅም እያላት የምትሰበስበው ገቢ በጣም ዝቅተኛ መሆኑንና በመዲናዋ ሕገወጥነትና ያለደረሰኝ የሚፈጸም ግብይትን ለመከላከል ከቢሮው ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ሐገሪቷን እንድትበለጽግ የንግዱ ማህበረሰብ ከመንግስት ጋር ተቀናጅቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ከደረሰኝ ግብይት ጋር በተያያዘ የተጀመሩ የቁጥጥር ተግባራ ከቢሮው ጋር በመቀናጀት በአግባቡ እንዲፈጸሙ ኮሚሽኑ በትኩረት የሚሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።
ከጉምሩክ አሰራር ጋር በተያያዘ ከንግዱ ማህበረሰብ የተነሱ አግባብነት ያላቸው ጥያቄዎችን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል።
የሐገራችንን በፍጥነት የማደግና ለድሕነት እድሜ መስጠት የሚወሰነው በንግዱ ማህበረሰብ ወይም በዜጎቿ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው ደገፋ በዘርፉ ያለው ሕገወጥ አሰራርን ለመፍታት ሚንስትር መስሪያ ቤቱ ከቢሮው ጋር በቅንጅት እየሰራና እያስተባበረ መሆኑን ገልጸዋል።
ውጤታማ ገቢ አሰባሰብ ! ለአዲስ አበባችን ብልፅግና !