የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ከዋና መስሪያ ቤቱ 17ቱን የግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች የስራ እንቅስቃሴ ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የሰርቪሊያንስ ካሜራ ቴክኖሎጂ ተግባሪያዊ አደረገ፡፡
ሰኔ 28 ቀን 2017ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፣ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በስሩ የሚገኙ 17 ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች የስራ እንስቃሴዎች ከማዕከል ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የሰርቪሊያንስ ካሜራ ቴክኖሎጂ ከኢኖቬዝንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በመተባበር ወደ ተግባር ማሸጋገሩ ታውቋል፡፡
ቢሮው ተግባሪያዊ ያደረገው የሰርቪሊያንስ ካሜራ ቴክኖሎጂ በሁሉም ቅርንጫፎች የሰራተኞች የስራ እንቅስቃሴ፣ የግብር ከፋዮች መስተንግዶና አገልግሎት አሰጣጥን ለመከታተልና ችግሮች ሲስተዋሉም ለማረም የሚያግዝ መሆኑ ተገልፆል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሰርቪሊያንስ ካሜራው ከማዕከል ሊተላለፉ የሚገባቸው መረጃዎችን በተመሳሳይ ሰዓት ለማድረስ እንዲሁም የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን በመከታተል እንዲታረሙ ለማድረግ ያስችላል ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት የቴክኖሎጂው የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቅቆ ወደ ተግባር የተሸጋገረ ሲሆን ሁለተኛው ምዕራፍ እስከ መስከረም ወር ለማጠናቀቅ እየተሰራም ይገኛል፡፡
በሁለተኛ ምዕራፉም ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ከማዕከል ወደ ሁሉም ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ድምፅን ያካተተ የቪዲዮ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ፣ ለግብር ከፋዮች ግንዛቤ የሚፈጥሩ አጫጭር መረጃዎችና ትምህርቶች ለመስጠት ይረዳል ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ 1 ከፍተኛ፣ 5 መካከለኛ፣ 11 አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ያሉት ሲሆን በስሩ ከ7 ሺህ በላይ ሰራተኞች የሚመራ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡