የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በአጭር ወራት ወደ ተግባር እያሸጋገራቸው ያሉ አሰራሮች በንግዱ ማህበረሰብ የተነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ያለውን ቁርጠኛ አቋም ማሳያ ናቸው ሲል የአዲስ አበባ ከተማ የንግድና ዘርፍ ም/ቤት አመራሮች ገለፁ፡፡
ሰኔ 26 ቀን 2017ዓ.ም. አዲስ አበባ፣ ገቢዎች ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት በመዘርጋት በንግዱ ማህበረሰብ የተነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ከመጪው ሀምሌ ወር 2017ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር ለማሸጋገር ባቀዳቸው አዳዲስ አሰራሮች ዙሪያ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድና ዘርፍ ም/ቤት አመራሮች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ የቢሮው ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ ቢሮው ከመጪው የግብር ማሳወቂያ ጊዜ ጀምሮ ፍትሃዊ የግብር አሰባበሰብ ስርዓትን ለመዘርጋት፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራሮች ለመከላከልና ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ በመስጠት ከግብር ከፋዮች የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተለዩ አዳዲስ አሰራሮችን ወደ ተግባር ለማሸጋገር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡
በቢሮው የችግሮችን ምንጭ በጥናት በመለየት ለመፍታት 24 አዳዲስ አሰራሮች ወደ ተግባር ለማሸጋገር እየሰራ ነው ያሉት ኃላፊው ከኦዲት ውሳኔዎች ጋር በተያያዘ የግልፀኝነት መጓደል የሚስተዋልባቸውን፣ ለሌብነትና ብልሹ አሰራር በር የሚከፍቱ የህግና የአሰራር ክፍተቶች ለማረም የሚያስችሉ አሰራሮች ይተገበራሉ ብለዋል፡፡
በቢሮው የተጀመረው የደረሰኝ ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለፅ በንግዱ ማህበሰረብ ከደረሰኝ ውጭ በተገዙ ምርቶች በሚመለከት የሚነሱ ጥያቄዎችን በቢሮው ምላሽ መስጠቱንም አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ ደረሰኝ ሊቀርብባቸው አዳጋች በሆኑ ጉዳዮች ወጪ አያያዝ በተመለከተም በአሰራር ለመመለስ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡
አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማልማትና ወደ ተግባር በማሸጋገርም የንግዱ ማህበሰረብ ከባለሙያዎች ስነ ምግባር፣ ከሌብነትና ብልሹ አሰራር ፣ ከፍትሃዊ የግብር አሰባሰብ ስርዓት አኳያ ለሚነሱ ቅሬታዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ቢሮው ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘም ለግብር ከፋዮች ምቹ የስራ አካባቢ ለማዘጋጀትና ግብር ከፋዮች ወደ ተቋሙ ሲመጡ በአግባቡ ሊስተናገዱ የሚችሉበት የስራ አካባቢ ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የንግዱ ማህበሰረብም ህገወጥ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ የገለፁት የቢሮው ኃላፊው ቢሮው ህጋዊ ነጋዴዎችን ለማበረታታት ህገወጦችን ደግሞ ተጠያቂ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድና ዘርፍ ም/ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሃራ መሐመድ በበኩላቸው ቢሮው የንግዱ ማህበሰረብ ቅሬታዎችን በአሰራር፣ በአደረጃጀትና በቴክኖሎጂ ለመፍታት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የሚያስመሰግነው ነው ብለዋል፡፡
የቢሮው አመራር ለዓመታት በንግዱ ማህበሰረብ ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎች በአጭር ጊዜ ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ እንዲመጡ በማድረግ ረገድ በኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቢሮው ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል እያደረገ ያለው ጥረት ም/ቤቱ ተባብሮ በመስራት እንዲሳካ የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡
በዕለቱ የተሳተፉ የአዲስ አበባ ከተማ የንግድና ዘርፍ ም/ቤት አመራሮች በበኩላቸው ቢሮው የንግዱ ማህበረሰብ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች ለመፍታት እየሄደበት ያለው አቅጣጫ ትክክለኛና ተስፋ የሚጭር ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡
በዕለቱም ከንግዱ ማህበረሰብ ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የቢሮው ከፍተኛ አመራሮች ምላሽና ማብራሪያም ሰጥተዋል፡