የከተማ አስተዳደሩ በ2017 በጀት ዓመት በገቢ ዘርፉ ለተመዘገበ ውጤት ተገቢው እውቅና መስጠቱ ለቀጣይ ተልዕኮ ስንቅ የሚሆን ነው ሲሉ የቢሮው አመራሮችና ሰራተኞች ገለፁ፡፡
ሀምሌ 6 ቀን 2017ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፣ ገቢዎች ቢሮ
ይህ የተገለጸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች በዛሬው ዕለት የቢሮው ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ ለአጠቃላይ ሰራተኞች የ2018 የገቢ ዕቅድ ለማሳካት ታቅደው ወደ ተግባር በተሸጋገሩ አሰራሮች ላይ የቪዲዮ ገለፃ ካደረጉ በኃላ በተካሄደ ውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡
በ17ቱም ቅርንጫፎች በተካሄደ የሰራተኞች ውይይት ላይ ውይይት ያካሄዱ ሰራተኞች እንደገለፁት ቢሮው በዘረጋቸው አሰራሮች ላይ ግልጸኝነት ለመፍጠር መድረክ መፈጠሩ የሚያበረታታና ወቅታዊነቱ የጠበቀ ነው ብለዋል፡፡
ቢሮው በ2017 በጀት ዓመት ለማስመዝገብ በቻለው ውጤትም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እውቅና በማግኘት ምስጋና መሰጠቱ ለቀጣይ ስራ የሚያበረታታን ነው ብለዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ የተሰጠ ዕውቅናም ለቀጣይ በጀት ዓመት ተልዕኮ እንደ ማበረታቻ ስንቅ በማድረግ ለስኬት የሚያተጋ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የቢሮው አመራሮችና ሰራተኞችም በበጀት ዓመቱ እንደ ከተማ የታቀደውን የ350 ቢሊዮን ብር ውስጥ በገቢዎች ቢሮ ሊሰበሰብ የታቀደውን የ256 ቢሊዮን ብር ለማሳካት ካለፈው በጀት ዓመት በቂ ትምህርት በመውሰድ ለከተማዋ ልማትና ዕድገት ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ይገባልም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩልም ቢሮውን ለስራ ምቹና የማድረግ ስራ በማጠናከር ለግብር ከፋዮም ለሰራተኛወም ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያም ግብር ከፋዩን በቅንነት ማስተናገድ ይገባናል ያሉት ሰራተኞቹ ገንዘብ ይዞ የሚመጣን ግብር በጥሩ ስነ ምግባር ማስተናገድ ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሌብነት የግብር ስርዓቱ ዋነኛ እንቅፋት መሆኑን በመጠቆም በየቦታው የሚገኙ ጥቂት ሌቦችን መታገል የሁሉም ሰራተኞች ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡