ቢሮው በካፒታል ዋጋ እድገት በሚገኝ ጥቅም ላይ በሚከፈል ግብር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮችና ለባለድርሻ መስሪያ ቤቶች ሰጠ

ቢሮው በካፒታል ዋጋ እድገት በሚገኝ ጥቅም ላይ በሚከፈል ግብር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮችና ለባለድርሻ መስሪያ ቤቶች ሰጠ ።

መጋቢት 26 / 2016 ዓ.ም የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ መድረኩን በከፈቱበት ወቅት እንደገለጹት ከተማችን አዲስ አበባ ትላልቅ የድርጅቶች ይዞታዎች የሚገኙባትና ግብይቶች የሚፈጸምባት ከተማ መሆኗን ገልፀው ከዚህ ዘርፍ ገቢዎች ቢሮ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ተቋማት በውክልና ገቢ እንደሚሰበስቡ ገልጸው እነዚህ ተቋማት ባማከለ መልኩ በአሰራር ዙሪያ ግልጽነት ለመፍጠር መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል ።

ለተገልጋዮች አገልግሎት አሰጣጥ ወይም መስተንግዶ ጋር በተያያዘ የአሰራር ወጥነት ችግሮች ምክንያት ዜጎች ፍትሐዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረግ ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመቅረፍ በእውቀት ላይ የተመሰረተ አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን የገለፁት ሀላፊው ይህን ዕድል በሚገባ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል ።

ሰልጣኞች ለስልጠናው ትኩረት በመስጠት በግንዛቤ እጥረት ፣ በቸልተኝነትና በብልሹ አሰራር ምክንያት የሚስተዋሉ ችግሮችን በዝርዝር በመወያየትና መግባባት በመፍጠር የገቢ አሰባሰቡ ውጤታማ እንዲያደርጉም አቶ አደም አሳስበዋል ።

የስልጠናው ዋነኛ ዓላማ የካፒታል ሀብቶችን በማስተላለፍ የሚገኝ ጥቅም ስለሚከፈል ግብር ገቢውን የሚሰበስቡ የተቋሙ አመራሮች እና የሚመለከታቸው ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የላቀ ግንዛቤ በመፍጠር ከዘርፉ ሊሰበሰብና ሊገኝ የሚገባውን ታክስ ገቢ በብቃትና በሀላፊነት ለመሠብሠብ እንዲቻል እና ወጥነት ያለው አተገባበር ለመዘርጋት መሆኑ ተመላክቷል ።

የስልጠናው መድረክ የመሩት በቢሮው የታክስ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘገየ በላይነህ በበኩላቸው ስልጠናውን የሰጡትን የፌደራል ገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ አማካሪ አቶ ዋሲሁን አባተን በተቋሙና በሰልጣኞች ስም አመሥግነው ስልጠናው በአሰራርና ከሕግ ማዕቀፎች ከመተግበር ጋር የተያያዙ ብዥታዎችን ለመፍታት ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር አሰልጣኞች በስራ ላይ ያጋጠሟቸው ችግሮችን ለመፍታት አጋዥ ነው ብለዋል

ከዚህ ስልጠናና የውይይት መድረክ በመነሳት በቀጣይ ስራዎቻችንን በጥልቅ በመገምገምና በመፈተሽ በታክስ አሰባሰብ የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች በመለየት ውጤታማ የገቢ አሰባሰብ ስራ ልንሰራ ይገባል ለዚህም በቁርጠኝነትና በተጠያቂነት መንቀሳቀስ ግድ ነው ሲሉ አቶ ዘገየ አሳስበዋል ።

ስልጠናውን በኢፌዴሪ የገንዘብ ሚንስቴር የታክስ አማካሪ አቶ ዋሲሁን አባተ ከነባራዊ ሁኔታ ጋር በተለይም ከመመሪያ ፣ ከህጎችና አሰራር አንፃር በማያያዝ ሰፋ አድርገው የካበተ ልምዳቸውንና ዕውቀታቸውን ተጠቅመው ሰጥተዋል ።

የካፒታል ሀብቶችን በማስተላለፍ በሚገኝ ጥቅም ላይ ስለሚከፈል ታክስ ግብር መመሪያዎችንና አሰራሮችን እንዲሁም መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ዕውነታ ማወቅም ግድ እንደሚል አቶ ዋሲሁን በስልጠናቸው ገልጸዋል ።

በአሰልጣኝነት የተሳተፉ ሰልጣኞች ስልጠናው እጅግ ሳቢ ፣ አቅም የሚፈጥር በስራ ላይ ለሚገጥሙን ተግዳሮቶች መፍትሔ ሰጪ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልፀው ያገኙትን ዕውቀት መሠረት አርገው እንደሚሰሩም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ።

በስልጠናው ላይ የኢፌዴሪ ገቢዎች ሚንስቴር ፣ የአዲስ አበባ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ተወካዮች ፣ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የዋናው መስሪያ ቤትና የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አመራሮች እና ዳይሬክቶሬቶች የአዲስ አበባ የመሬት ይዞታ፣ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የተወከሉ አመራርና ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል።

የላቀ ገቢ ለአዲስ አበባችን ሁለንተናዊ ብልጽግና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *