በአዲስ አበባ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 108 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል

በአዲስ አበባ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 108 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል

***********************

(ኢ ፕ ድ)

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 108 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አደም ኑሪ ለኢዜአ እንዳሉት ቢሮው በ2016 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 109 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 108 ቢሊዮን ብር የሰበሰበ ሲሆን አፈጻጸሙም 98 ነጥብ 5 በመቶ ነው።

ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ45 በመቶ እድገት ወይም የ34 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል።

በ2015 በጀት ዓመት በአጠቃላይ ከተሰበሰበው 107 ቢሊዮን ብር ገቢ ጋር ሲነጻጸር ደግሞ የ1 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው ብለዋል።

ቢሮው ገቢውን የሰበሰበው ከቀጥታ ታክስ፣ ቀጥተኛ ካልሆኑ ታክስ አገልግሎቶች፣ ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ እና ሌሎች መሆኑን አስረድተዋል።

ሕገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል፣ የታክስ አከፋፈል አገልግሎትን ለማሻሻል በዲጂታል የታገዙ አሰራሮች እየተተገበሩ መሆኑንም አቶ አደም ገልጸዋል።

ቢሮው በሀሰተኛ ደረሰኝ የሚፈፀም ግብይትን ለመቆጣጠር ባደረገው ክትትል ከ5 ሺህ በላይ ግብይቶች በሀሰተኛ ደረሰኝ መፈጸማቸውን ማረጋገጡን አስታውቀዋል።

በሀሰተኛ ደረሰኝ ግብይት ሲፈፅሙ የተገኙ ግብር ከፋዮች ላይም 225 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ቅጣት በማስከፈል አስተዳደራዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ140 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፥ ለዚህም ስኬት ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግና ግብር ከፋዩም በታማኝነት ግብሩን እንዲከፍል አሳስበዋል።

የምንከፍለው ግብር ለራሳችን ጥቅም መሆኑን መገንዘብ ይገባል ያሉት ቢሮ ኃላፊው፤ አዲስ አበባ የምታመነጨውን ያህል ገቢ ለመሰብሰብ የግብር ከፋዩ፣ የአመራሩና የማህበረሰቡ ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ መሆኑንም እንዲሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *